ለደቡብ ሱዳንና ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለደቡብ ሱዳንና ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2016(ኢዜአ)፡- ለደቡብ ሱዳንና ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለፀ።
ኢትዮጵያ በኃይል ሽያጭ በኩል እየሰራቻቸው ያሉ ተግባራት ለምስራቅ አፍሪካ አገራት የኃይል ትስስር አስተዋፅዖ ያለው መሆኑም ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለሱዳን፣ ለጂቡቲና ለኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ እያከናወነች ነው።
አሁን ላይ ደግሞ ለሌሎች ተጨማሪ ጎረቤት አገራት ሽያጭ ለማከናወን እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል።
ይህንንም ተከትሎ ለደቡብ ሱዳን ኤሌክትሪክ ሽያጭ ለማከናወን የደቡብ ሱዳን የኢነርጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር በ2014 ዓ.ም ሥምምነት መፈራረማቸውን አንስተዋል።
በሥምምነቱ መሠረት አሁን ላይም ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ ሱዳን ኤሌክትሪክ ማስተላለፍ የሚቻልበትን ሁኔታ የሚያጠና የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን ተዋቅሮ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።
የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን የሚያቀርበውን ዝርዝር ጥናት መሠረት በማድረግ የመስመር ዝርጋታና ከማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ጋር የተገናኙ ሥራዎች ይሰራሉ ነው ያሉት።
ሥራዎቹ በሁለት ምዕራፍ ለማከናወን መታቀዱን አንስተው የመጀመሪያው ከጋምቤላ ሁለት ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እስከ ደቡብ ሱዳን ማላካል 357 ኪሎ ሜትር የ230 ኪሎ-ቮልት መስመር ዝርጋታ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ ደግሞ ከቴፒ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እስከ ጁባ 700 ኪሎ ሜትር ከ400 እስከ 500 ኪሎ-ቮልት የሚዘረጋ የኤሌክትሪክ መስመር መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተመሳሳይ ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።
ሁለቱ አገራት የማይዋሰኑ በመሆናቸው የኢትዮጵያ-ኬንያ የኃይል መስመር በመጠቀም ሽያጩን ለማከናወን መታቀዱንም ተናግረዋል።
ለዚህም ከታንዛኒያ ጋር የኃይል ሽያጭ እንዲሁም ከኬንያ ጋር ግሪዱን ተጠቅሞ ለማስተላለፍ የሚያስችል ሥምምነት እንደሚደረግም አንስተዋል።
ከታንዛኒያ ጋር ከዋጋና ማስተላለፍ ጋር በተገናኘ ድርድር መጀመሩንና እስከ ተያዘው በጀት ዓመት አጋማሽ ለማጠናቀቅ መታቀዱን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በኃይል ሽያጭ በኩል እየሰራቻቸው ያሉ ተግባራት ለምስራቅ አፍሪካ አገራት የኃይል ትስስር አስተዋፅዖ ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል።