ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን የፕላስቲክ ምርት ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ለመተካት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን የፕላስቲክ ምርት ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ለመተካት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን የፕላስቲክ ምርት ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ለመተካት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የፕላስቲክና ጎማ አምራቾች ማህበር ዓመታዊ ጉባኤውን ዛሬ በአዲስ አበባ አካሂዷል።
የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ምንተስኖት ለማ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ፕላስቲክ ለግብርና ልማት የውሃ መሳቢያ ፓምፕ፣ለመኪና መገጣጠሚያ ግብዓት፣ ለቤት ግንባታ፣ ለቤትና የቢሮ እቃዎች፣ ለአይሲቲ መሰረተ ልማቶች ሟሟያና ለሌሎችም አገልግሎቶች እየዋለ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ4 ሺህ በላይ የፕላስቲክና ጎማ ምርት ላይ የተሰማሩ አምራቾች ቢኖሩም ካላቸው የማምረት አቅም አኳያ የምርት ምጣኔያቸው አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
አምራች ኩባንያዎችን ጨምሮ ባለድርሻ ተቋማት በጉዳዩ ላይ ያላቸው የግንዛቤ ክፍተትና ቅንጅታዊ አሰራር አለመዳበርም ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ውጤት እንዳይገኝ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በዚህም የተነሳ ከፍተኛ በሆነ የውጭ ምንዛሪ የፕላስቲክ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እየገባ መሆኑን በማንሳት፤ ይህም አገሪቱን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረገ ይገኛል ነው ያሉት።
ማህበሩ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ገንዘብ ከውጭ የምታስገባውን የፕላስቲክ ምርት ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ለመተካት የተለያዩ አማራጮች ላይ መሰረት ያደረጉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የፕላስቲክና ጎማ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ዮናስ አባተ በበኩላቸው፤ መንግስት የፕላስቲክ የማምረት አቅምን ለማሳደግ ከግሉ ዘርፍ ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።
በተለይም ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት ለሚሰሩና በዘርፉ ከፍተኛ የስራ ዕድል ለሚፈጥሩ አምራቾች የተለያዩ የማበረታቻ ስርዓቶች በመዘርጋት ላይ መሆናቸውን ነው ያስረዱት።
ለአብነትም የፕላስቲክ አምራቾች ያሉባቸውን ጫናዎች ለማቃለል የጥሬ እቃ ቀረጥ ቅነሳ መደረጉን አንስተዋል።
ከዚህም ባለፈ መልሰው ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ውጤቶችን እንደ ግብዓት በመጠቀም ማምረት እንዲችሉም መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።
ዶክተር ዮናስ አክለውም የኢትዮጵያ የፕላስቲክና ጎማ አምራቾች ማህበር ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከርና ውስጣዊ አቅምን አሟጦ መጠቀም ላይ እንዲያተኩር ጠይቀዋል።