ኢትዮጵያ ለዘመናት ከባህር በር ጋር ካላት ቁርኝትና ታሪካዊ ዳራ አኳያ ጥያቄውን ማንሳቷ ትክክለኛና ልንሰራበት የሚገባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለዘመናት ከባህር በር ጋር ካላት ቁርኝትና ታሪካዊ ዳራ አኳያ ጥያቄውን ማንሳቷ ትክክለኛና ልንሰራበት የሚገባ ነው
ጋምቤላ ፤ ጥቅምት 10/2016 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ ለዘመናት ከባህር በር ጋር ካላት ቁርኝትና ታሪካዊ ዳራ አኳያ ፍላጎቷን በሕጋዊ መንገድ ለማግኘት ጥያቄውን ማንሳቷ ትክክለኛና ልንሰራበት የሚገባ ነው።
የሐረማያ፣ የጅማ እና የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን የሌሎች አገሮችን ሉዓላዊነት በማይነካ መልኩ ወደቦችን በስምምነት፣ በመደራደርና በመተሳሰብ ለመጠቀም ጠንክሮ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የታሪክ ምሁራን መካከል በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ረታ ዱጉማ፤ ኢትዮጵያ ለዘመናት አዱሊስ፣ ምጽዋ እና አሰብ የተባሉ የባህር በሮችን እያለማች ስትጠቀም ቆይታለች።
የኋላ ታሪክ እንደሚያሳየውም አገሪቱ ያለወደብ የቆየችበት ጊዜ እንዳልነበር ጠቅሰው፣ለብዙ ዘመናትም ከእነዚህ ወደቦች ጋር የነበራት ቁርኝት ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለብዙ ዘመናት በእነዚህ ወደቦች ላይ ገንዘቧን ማፍሰሷን ያመለከቱት ዶክተር ረታ፣ በ1950ዎቹ የአሰብ ወደብን በደንብ ማልማቷን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በተባበሩት መንግስታት ኮንቬንሽን መሰረት የባህር በር የሌላቸው አገሮች ወደቦችን እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ የተቀመጠ ስምምነት መኖሩን የገለጹት ዶክተር ረታ፣ በእዚህ ማዕቀፍ መሰረት የሌላ አገርን ሉዓላዊነት በማይነካ መልኩ በመነጋገርና በስምምነት ወደቦችን መጠቀም እንደሚገባ መክረዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ከተቦ አብዲዮ በበኩላቸው ታሪክን ጠቅሰው እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ አዱሊስ የተባለ ወደብ ነበራት።
ከእዚህ በመነሳት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት እያሳየች ያለው ፍላጎት አግባብነት ያለውና ህጋዊ ጥያቄ መሆኑን ጠቁመዋል።
ወደብ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው የሚለውን ጥያቄ በጥንቃቄ ማየት ይገባልም ብለዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ የታሪክ ተማሪና የጋምቤላ ትምህርትና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የታሪክ መምህር በየነ ሐመረጥበብ በበኩላቸው፣ አሰብ ወደብ በወቅቱ ኢትዮጵያ አልምታ ስትጠቀምበት እንደነበር አስታውሰዋል።
የባህር በር ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዕድገት ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ ኢትዮጵያ ያነሳችው የባህር በር ፍላጎት አግባብነት ያለው መሰረታዊና ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ከዓለም አቀፍ ህጎችና ስምምነቶች አኳያ ሲታይም ተቀባይነት እንዳለው ነው መምህር በየነ ያብራሩት።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1952 ባሳለፈው የውሳኔ ሃሳብ ቁጥር 390/5 መሠረት የባሕር በር ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።