በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተስተዋለው የጉንፋንና ኢንፍሉዌንዛ በሽታ እንዳይስፋፋ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል- ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተስተዋለው የጉንፋንና ኢንፍሉዌንዛ በሽታ እንዳይስፋፋ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል- ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2016(ኢዜአ)፡- በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተስተዋለው የጉንፋንና ኢንፍሉዌንዛ በሽታ እንዳይስፋፋ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።
የጉንፋን እና መሰል ወረርሽኞች የዝናብ ወራት ማለፉን ተከትሎ በጥቅምት እና ኅዳር ወቅት ላይ በአብዛኛው ጊዜ እንደሚከሰት መረጃዎች ያመላክታሉ።
በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቫይረሱን በመሳልና በማስነጠስ ወደ ሌላኛው ሰው ሊያስተላልፉ ይችላሉ፤ ይህም ሆኖ ሕክምና ካገኘ በቀላሉ ሊድን የሚችል በሽታ መሆኑም ይነገራል።
የጤና ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው የዳሰሳ ጥናት አዲስ አበባን ጨምሮ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የጉንፋንና ኢንፍሉዌንዛ በሽታ መከሰታቸውን አረጋግጧል።
ኢዜአም ጉዳዩን አስመልክቶ ከጤና ሚኒስቴር የኮቪድ-19 ምላሽ ግብረ-ኃይል ዋና አስተባባሪ ዶክተር መብራቱ ማሴቦ ጋራ ቆይታ አድርጓል።
ዶክተር መብራቱ ማሴቦ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ከጥቅምት ወር መጀመሪያ ጀምሮ በአንዳንድ የሀገሪቷ አካባቢዎች የጉንፋንና ኢንፍሉዌንዛ በሽታ መከሰቱን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ በመሆን በ2 ሺህ ያህል ናሙናዎች ላይ ባደረገው ምርመራም የበሽታውን መከሰት ማረጋገጡን በማንሳት።
በሽታው ሕዝብ በሚበዛባቸው በተለይም ትምህርት ቤቶች፣ የገበያ ሥፍራዎች፣ የእምነት ቦታዎች በስፋት የመሠራጨት ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
በከተሞች እና ከፍተኛ መቀራረብ ባለባቸው የመኖሪያ ሥፍራዎች ጭምር የመስፋፋት አዝማሚያ ሊኖረው እንደሚችል አብራርተዋል፡፡
የትንፋሽ አቅም ማነስ፣ የሰውነት መቆረጣጠም እና የድካም ስሜቶች ከሕመሙ ምልክቶች መካከል ናቸው ብለዋል፡፡
ቫይረሱ ሳምባ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥርበት ደረጃ ሲደርስ ሳል፣ ከፍተኛ የሆነ የትንፋሽ ማጠርና ሌሎች ምልክቶች እንደሚስተዋሉ ገልጸው፤ እነዚህ ምልክቶች የታዩበት ግለሰብ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ሕክምና ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።
ሕብረተሰቡ እጅ በመታጠብ አፍና አፍንጫን በመሸፈን በሽታውን በቀላሉ መከላከል እንደሚችል አብራርተዋል።
በበሽታው የተያዙ ሰዎች ሥርጭቱ እንዳይስፋፋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ በቂ እረፍት በመውሰድ፣ ፈሳሽና ትኩስ ነገሮች በመጠቀምና ተገቢውን ሕክምና ማግኘት እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል፡፡
የጤና ባለሙያዎች የሚሰጧቸውን ምክረ-ሃሳቦችን በመተግበር፣ በርና መስኮቶችን በመክፈት በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖር በማድረግ መከላከል እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡