ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር የማግኘት መብት አላት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር የማግኘት መብት አላት
ድሬዳዋ/ ሆሳዕና ፤ ጥቅምት 10 /2016 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህና ባለው ታሪካዊ ዳራ የባህር በር የማግኘት መብት አላት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የባሕር በር አስፈላጊነትን አስመልክተው ገለጻ ማደረጋቸው ይታወሳል። በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በመልካዓ ምድርና በኢኮኖሚ ላይ በመመስረት የባህር በር ጥያቄ የማንሳት ሕጋዊ መብት እንዳላት የተባበሩት መንግስታትን ቻርተርና ስምምነት በመጥቀስ ያብራሩት ነጥብ ነው።
የባህርተኝነት ራዕይ መፍጠርና ማዳበር፣ ድንበር ተሻጋሪ የማህበራዊ ትስስርን ማጎልበት፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማሳደግና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በማብራሪያቸው አጽንኦት የሰጡት ጉዳይም ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ ኢዜአ የድሬዳዋና የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ከሆኑት ከፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን ጋር ቆይታ አድርጓል።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና የዓለም አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት መምህር ሱራፌል ጌታሁን እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የባህር በሯን በማጣቷ ለወደብ ኪራይ ከፍተኛ ገንዘብ እያወጣች መቆየቷን ጠቁመዋል።
ይህም በአገሪቷ ላይ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫና እንዲፈጠር ማድረጉን ጠቅሰው፤ የባህር በር ጉዳይ ለዓመታት ተዘንግቶ ቢቆይም አሁን ጥያቄ መነሳቱና አጀንዳ ሆኖ መምጣቱ ተገቢነት እንዳለው አስረድተዋል።
በአፍሪካ ቀንድና ቀይ ባህር አካባቢ የሃያላን አገሮች ትልቁ የኢኮኖሚ ኮሪደርና የስበት ማዕከል ሆኖ አካባቢውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ሽኩቻ የሚያደርጉበት እንደሆነ ያመለከቱት መምህር ሱራፌል፤ ይህም በአካባቢው ፖለቲካዊ ጫና እንዲበረታ ማድረጉን ገልጸዋል።
በቀጣናው ባለው ሃብት አጠቃቀም ላይ ኢትዮጵያ ባይተዋር መሆን እንደሌለባትና ድርሻ ሊኖራት እንደሚገባም አክለዋል።
ይህ ታሪካዊ ዳራ እንዳለም ሆኖ በዓለም አቀፍ ህግ መርህ መሰረትም አገሪቷ የወደብ ባለቤት የመሆን መብቷ ማስከበር እንድትችል "የህግ ፣ የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት አጥኚዎች ጨምሮ ሌሎችም ኢትዮጵያዊ ምሁራን መስራት አለብን" ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ኢትዮጵያ ሰጥቶ በመቀበል መርህ የባህር በር የማግኘትና የመጠቀም መብት እንዳላት አስረድተዋል።
በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ የህዝብ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር አባተ አንሺሶ በበኩላቸው፤ በታሪክ አጋጣሚ ወደብ አልባ የሆነችው ኢትዮጵያ ከአገር ለሚወጡና ለሚገቡ እቃዎች የወደብ ኪራይ በመክፈል ሁለንተናዊ እድገቷን ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።
መንግስት በዘላቂነት ከባህር በር ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አጀንዳና ጥያቄ አድርጎ ማንሳቱ ተገቢና በምክንያትነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ እንዲያገኝ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት በዲፕሎማሲ ዘዴ መሞገትና ማስረዳት እንደሚገባ ነው ምሁራኑ የሚገልጹት።
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መርህ የባለ ብዙ ወገን የትብብር ግንኙነትን የሚከተልና ከምንም በላይ ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስቀድም ነው።