የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ በመሆኑ የጋራ አቋም መያዝ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ በመሆኑ የጋራ አቋም መያዝ ይገባል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 10/2016 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጋራ አቋም በመያዝ የበኩላቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የባህር በርን በተመለከተ በቅርቡ ያደረጉት ገለጻ ትክክለኛና የሚደገፍ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ፖለቲከኞች ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሄር ፓርቲያቸው የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት ይጠበቃል ብለዋል።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የባህር በርን በተመለከተ ያነሱት ሀሳብ ትክክለኛና የሚደገፍ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደዚህ አይነት ብሔራዊ ጥቅምን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያውያን የጋራ አቋም መያዝ እንደሚገባቸውም ነው ያነሱት።
ለዚህ ደግሞ ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ በተለይ የውስጥ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ልምምድ መዳበር እንዳለበት ተናግረዋል።
የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ጌትነት ወርቁ በበኩላቸው ትውልዱ ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መብት እንዳላት በአግባቡ ሊረዳ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበራት ስልጣኔና ገናና ስም የባህር በር መኖርን ተከትሎ መምጣቱንም አስታውሰዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማት ለማረጋገጥ የባህር በር ተጠቃሚነት ጉዳይ በትውልዱ ውስጥ ማስረፅ ይገባል ነው ያሉት።
የባህር በር ጥያቄ የህልውና ጉዳይ እንደመሆኑ በተደጋጋሚ ሊነሳና በሁሉም ዘንድ አጀንዳ መሆን አለበት ብለዋል።
በፍጥነት እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሸከም የሚችል የባህር በር መኖር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ መያዝና መነጋገር አለበት ነው ያሉት።
የባህር በር ጉዳይም ሆነ ሌሎች የልማት አጀንዳዎች እውን የሚሆኑት በትብብር መሆኑን ጠቅሰው መንግስትን ጨምሮ ሁሉም አካላት ሰላም እንዲረጋገጥና አንድነት እንዲጠናከር መስራት አለባቸው ብለዋል።
ፖለቲከኛው ዶክተር ተሻለ ሰብሮ በበኩላቸው የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ በበጎ የማይመለከቱ አካላት፤ አጀንዳውን ወዳልተፈለገ መንገድ ለመውሰድ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላት ግንኙነት ሰላማዊና በትብብር ላይ የተመሰረተ መሆኑን በማንሳት፤ የባህር በር ጥያቄዋም በጋራ አብሮ መልማትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣናው የጀመረቻቸውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስሮች ለማሳደግ የበለጠ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ለዚህ ስኬትም የባህር በር ጥያቄን በጠንካራና ጥበብ በተሞላበት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እውን ለማድረግ እያንዳንዱ ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።