በአገራዊ የጋራ ማንነቶች፣ ጥቅሞችና እና እሴቶች ላይ መግባባት ለዘላቂ ሰላምና ልማት መሰረት ነው-የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታየ ደንደአ - ኢዜአ አማርኛ
በአገራዊ የጋራ ማንነቶች፣ ጥቅሞችና እና እሴቶች ላይ መግባባት ለዘላቂ ሰላምና ልማት መሰረት ነው-የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታየ ደንደአ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 10/2016 (ኢዜአ) ፦ በአገራዊ የጋራ ማንነቶች፣ ጥቅሞችና እና እሴቶች ላይ መግባባት መፍጠር ለዘላቂ ሰላምና ልማት መሰረት መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታየ ደንደአ ገለጹ።
የሰላም ሚኒስቴር "የሰላምና የሀገር ግንባታ መሰረታውያን፥ ሀገራዊ ጥቅሞች፣ የጋራ ማንነቶች፣ ሀገራዊ እሴቶችና ሴኩላሪዝም" በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታየ ደንደአ፣ የክልሎች ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊዎች፣ ምሁራን እና ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች እንግዶች እየተሳተፉ ነው።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታየ ደንደአ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዓለም ታሪክ በአገረ መንግስት ምስረታና ሉዓላዊ የግዛት አንድነታቸውን ጠብቀው ከቆዩ ጥንታዊ አገራት መካከል አንዷ ናት።
ብዝኃ ማንነት ያላቸው ዜጎቿም ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን በአንድነት በመቋቋም በአንድ ጥላ ስር አብረው መኖራቸውን ገልጸዋል።
በሁሉም የአገሪቷ ማዕዘናት ጠንካራ ማህበራዊ እሴትና መስተጋብር እንዳለ በመጠቆም፥ እነዚህን እሴቶች በማጠናከር ረገድ ግን ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ አንስተዋል።
የነጠላ እና ንዑሳን አጀንዳ በስፋት እየተቀነቀነና እየተስተጋባ መምጣቱን ተከትሎም በሚከሰቱ ግጭቶች በዜጎች ላይ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።
የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ የሚፈልጉትን ተልዕኮ ለማስፈጸም ያልሞከሩት ነገር የለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ዛሬም ድረስ የዜጎችን አንድነት ለማላላት ጥረት ሲያደርጉ እንደሚስተዋል አንስተዋል።
ቀጣይነት ያለው የጋራ አገረ መንግስት ለማስቀጠል በአገራዊ የጋራ ጥቅሞችን፣ ማንነቶችን እና እሴቶች ላይ መግባባት መፍጠር ለዘላቂ ሰላምና ልማት መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የብዝሃ ማንነት ምድር በመሆኗ በየማህበረሰቡ የሚገኙ መልካም እሴቶችን ለአገር ሰላም፣ ደህንነትና ልማት እንዲውሉ ለማስቻል ጥናት መደረጉን አስታውቀዋል።
በመድረኩ የሰላምና የሀገር ግንባታ መሰረታውያን፣ በሀገራዊ የጋራ ጥቅሞች፣ ማንነቶች፣ እሴቶች እና በሴኩላሪዝም ላይ ያተኮሩ የመነሻ ጽሑፎች ቀርበው ምክክር እየተደረገባቸው ይገኛል።