ከስደት ተመላሽ ዜጎች ባፈሩት ሀብት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ድጋፍ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከስደት ተመላሽ ዜጎች ባፈሩት ሀብት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ድጋፍ እየተደረገ ነው
ሆሳዕና ጥቅምት 9/2016 (ኢዜአ) :-ከስደት የተመለሱ ዜጎች ባፈሩት ሀብት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ እንዲሆኑ በጥናትና ምርመር የታገዘ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ፍልሰት ለልማትና ለእኩልነት ፕሮጀክት (MIDEQ) አስታወቀ።
በአሁኑ ወቅት ከ1 መቶ ሃያ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በደቡብ አፍሪካ ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመት ሚዴቅ የተሰኘ በስደተኞች ላይ ያተኮሩ መረጃዎችን የሚያሰራጭ ድረገፅ አመልክቷል።
አብዛኞቹ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረጉ ፍልሰቶች ዋነኛ ምንጭና መነሻ የደቡቡ የሃገራችን ክፍል በተለይም ከሃዲያ ዞን ሆሳዕና አካባቢ እንደሆነም ይታወቃል።
ፕሮጀክቱ ከዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በስደተኞች ዙሪያ አመርቂ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ለመምከርና ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተዘጋጀ መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሄዷል።
በዚህ ወቅት በፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ አስተባባሪ ዶክተር ደረጀ ፈይሳ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት ፕሮጀክቱ በዓለም ላይ በ12 ሀገራትና በስድስት የፍልሰት ኮሪደሮች ላይ እየሰራ ይገኛል።
በፍልሰትና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ የጥናትና ምርምር ሥራ ከማከናወን ባለፈ በህገ ወጥ ፍልሰት ምክንያት በተለያዩ ኮሪደሮች የተያዙና የታሰሩ ዜጐችን ደህንነት ለማስጠበቅም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሀገሪቱ ከፍተኛ ፍልሰት ከሚስተዋልባቸው አካባቢዎች አንዱና ዋነኛው ሀድያ ዞን መሆኑን ጠቁመው ችግሩን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር ፕሮጀክቱ ከዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቤተሰባቸውን በመደገፍና በሀገር ውሰጥ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ለልማትና ዕድገት አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ገልጸው በዚህ ረገድ በሀድያ ዞን እየተመዘገበ ያለው ለውጥ ለዚያ ማሳያ እንደሚሆን አውስተዋል።
ተግባሩን በተሳለጠ መልኩ ለመከወን በዞኑ በጥናት ላይ የተመረኮዘ የኢንቨስትመንት ጋይድ በፕሮጀክቱ መዘጋጀቱን ጠቅሰው በቀጣይ ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት ከአካባቢው ተወላጆች ጋር መግባባት ላይ ለመድረስ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
የፕሮጀክቱ ምክትል አስተባባሪ ፕሮፌሰር ለውስ ሄርንስ በበኩላቸው የሀገሪቱ ወጣቶች ውጭ ሀገር በመሄድ ሰርቶ ለመለወጥ ያላቸው ፍላጎት የማያቋርጥ እንደሆነ በፕሮጀክቱ በተካሄደ ጥናት መረጋገጡን ገልጸዋል።
በስደት ላይ የሚገኙ ወጣቶች ያፈሩትን ሀብት በአግባቡ እንዲጠቀሙ ከማድረግ ባለፈ በተለያዩ አዋጪ የስራ መስኮች በመሰማራት ለሌሎች ወገኖቻቸው የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈለግ አስገንዝበዋል።
በፍልሰት ተግዳሮቶችና ስኬቶች ዙሪያ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ማከናወንና የዩኒቨርስቲውን ምሁራን ማጎልበት የመድረኩ ዓላማ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የምርምርና ማህበረሰብ አጋርነት ዳይሬክተር ዶክተር አበበ ሎላሞ ናቸው።
የአካባቢው ተወላጆች ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት በፍልሰት የሚኖሩበትና ከራሳቸው አልፈው አካባቢዉን ለማልማት የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ ዩኒቨርስቲው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በጥናትና ምርምር የተደገፈ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝም አክለዋል።
ለአንድ ቀን በተሰናዳው መርሃ ግብር ላይ የዩኒቨርስቲው ምሁራን፣ የፕሮጀክቱ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።