ቀጥታ፡

መንግስት የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ስራን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ዘርፉን ይበልጥ ለማዘመን በትኩረት ይሰራል- ዶክተር አለሙ ስሜ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2016(ኢዜአ)፦መንግስት የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ስራን በቴክኖሎጂ በመደገፍና ምቹ የስራ አካባቢን በመፍጠር ዘርፉን ይበልጥ ለማዘመን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣንና የኢትዮጵያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ማህበር ዓለም አቀፍ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ቀንን በቦሌ ዓለም አቀፍ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል አክብረዋል።

በመረሃ-ግብሩ ላይ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር አለሙ ስሜ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው እንዲሁም የተለያዩ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።

በመርሃ ግብሩም አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ደህንነቱ የተጠበቀ የበረራ አገልግሎት እንዲኖር በማስቻል ረገድ የዘርፉ የጀርባ አጥንት ሆነው በመስራት ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሚያነሷቸው ጥቅማ ጥቅምን ጨምሮ ምቹ የስራ አካባቢ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡


 

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር አለሙ ስሜ፤ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ላለው የሀገሪቷ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የላቀ ሚና እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ሙያው በስራ ሰዓት ያልተገደበ በመሆኑ በዘርፉ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በልዩ ትኩረት ሰራቸውን እንደሚያከናውኑ ጠቅሰው፤ ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

መንግስት ለሙያተኞቹ ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠርን ጨምሮ የስራ ሁኔታቸውን የሚያሻሽሉ ሌሎች ተግባራትን በማከናወን ረገድ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ ፣ውስብስብና ተለዋዋጭ በሆነው የአቪዬሽን መስክ የአየር ትራፊክ ባለሙያዎች ሚና የማይተካ እንደሆነ አንስተዋል።

ባለስልጣኑ በሙያው ተሰማርተው ያሉ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች አቅም በፈቀደ አግባብ ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ስራን በተሻለ ቴክኖሎጂ ለመደገፍ ከሲቪል አቪዬሽ ባለስልጣን ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚሰጠው አገልግሎት ደህንነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ቀን በየዓመቱ በፈረንጆቹ ጥቅምት 20 የሚከበር ሲሆን ዘንድሮም ለ101ኛ ጊዜ ተከብሯል፡፡

እለቱ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ለአቪዬሽን ኢንዳስትሪ እያበረከቱ ላለው አስተዋጽኦ እውቅና በመስጠት የሚከበር ሲሆን፤ በዛሬው እለትም በሙያው የላቀ አበርክቶ ላደረጉ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በየቀኑ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በአማካይ 100 ሺህ ለሚሆኑ በረራዎች የአየር ትራፊክ ቁጥጥር አገልግሎት እንደሚሰጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም