ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የደምና ኅብረ- ህዋስ ባንክ በቂ የደም ክምችት ባለመኖሩ በጎ ፈቃደኞች በቋሚነት ደም በመለገስ ምላሽ እንዲሰጡ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2016(ኢዜአ)፡-  በአገሪቱ በቂ የደም ክምችት ባለመኖሩ በጎ ፈቃደኞች  በቋሚነት ደም በመለገስ ምላሽ እንዲሰጡ የኢትዮጵያ የደምና ኅብረ- ህዋስ ባንክ  ጥሪ አቀረበ።
 

የካንሰር ታካሚዎች፣ ወላድ እናቶችና ሌሎች ታማሚዎችን ሕይወት ለማትረፍ የበጎ ፈቃደኞች ደም ልገሳ ተግባር በእጅጉ እንደሚያስፈልግ ይታወቃል።


 

የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት  አገራት ካላቸው አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር ውስጥ 1 በመቶ የሚሆነው በቋሚነት ደም በመለገስ  ተግባር ላይ መሳተፍ እንዳለበት ያስቀምጣል።

 

በኢትዮጵያ ደግሞ በቋሚነት በደም መለገስ የበጎ ፈቃድ ስራ ተሳታፊ የሆነው የማሕበረሰብ ቁጥር ከግማሽ ሚሊየን በታች በመሆኑ በተደጋጋሚ የደም እጥረት እንደሚገጥም ነው  የሚገለፀው።

 

የኢትዮጵያ የደምና ኅብረ- ህዋስ ባንክ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጤናዬ ደምሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤  በሀገሪቱ በቋሚነት ደም የሚለግሰው በጎ ፈቃደኛ  ቁጥር በሚፈለገው ልክ አይደለም ።

 

በዚህም ባንኩ የሆስፒታሎች የደም ፍላጎትንና አቅርቦት ባለመመጣጠኑ ጥያቄዎችን በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ ተግዳሮቶች እየገጠመው መሆኑን ነው የሚናገሩት።

 

በቋሚነት ለባንኩ ደም የሚለግሱት ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ ከነሱ ጋር በተያያዘ በአብዛኛዎቹ በክረምት ወቅት ሲዘጉ የደም እጥረት እንደሚገጥም ነው የተናገሩት።

 

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ባንኩ  በቂ የሆነ የደም ክምችት እንደሌለው አመልክተው፤ህብረተሰቡ በቋሚነት ደም እንዲለግስ ጥሪ አቅርበዋል። 

 

የአገሪቱ  ዓመታዊ የደም ፍላጎት አንድ ሚሊዮን ዩኒት ያህል ቢሆንም በአገር አቀፍ ደረጃ በ2015 ዓ ም ከለጋሾች  የተገኘው ደም ከ353 ሺህ ዩኒት እንደማይበልጥ መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም