ቀጥታ፡

የባህር በር መኖር የምርት ግብዓትን በተፈለገ ጊዜ ከማግኘት ባሻገር በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆንም የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2016(ኢዜአ)፦የባህር በር መኖር የምርት ግብዓትን በተፈለገ ጊዜና በተመጣጣኝ ዋጋ ከማግኘት ባሻገር በዓለም ገበያም ተወዳዳሪ የሚያደርግ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የባሕር በር ጠቀሜታን አስመልክተው ገለጻ ባደረጉበት ወቅት የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን መረጃ ጠቅሰው የአንድ አገር የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት (ጂዲፒ) ከ25 እስክ 30 በመቶ የባሕር በር ስለመሆኑ አንስተዋል።

"ለምሳሌ ኢትዮጵያ 100 ቢሊዬን ከሆነ 'ጂዲፒዋ' ዓይኗ እያየ 20 ቢሊዬን 30 ቢሊዬን ትታለች ማለት ነው" ሲሉ የባሕር በር አልባ መሆን የሚያስከትለውን ጉዳት አብራርተዋል።

ይሁንኑ መነሻ በማድረግ ከሀረማያ፣ ከሀዋሳ፣ ከድሬዳዋና ከመደወላቡ ዩኒቨርሲቲዎች የኢኮኖሚ ዘርፍ መምህራንና ተመራማሪዎች ጋር ኢዜአ ቆይታ ያደረገ ሲሆን፤ ምሁራኑም የዶክተር ዐቢይን ሀሳብ ይጋራሉ።

በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ምጣኔ ሃብት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ከተማ በቀለ፣ ለአንድ አገር እድገት "የባሕር በር ወሳኝና ቁልፍ ሚና ይጫወታል" ይላሉ።

በተለይም የባሕር በር ከምርትና ምርታማነት፣ ከምርት ግብዓት፣ ከምርት ሂደት እንዲሁም ራሱ በምርቱ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አለው።

''በጥቅሉ ከምጣኔ ሀብት አኳያ ሲቃኝ የባሕር በር ጉዳይ ለአንድ አገር ጉልህ ድርሻ የሚያሳርፍ ነው'' ያሉት ዶክተር ከተማ፤ ለአብነት የኢትዮጵያ ግብርናን ለመለወጥና ለማሳደግ ከፍተኛ የግብዓት አቅርቦት እንደሚፈልግ አውስተዋል።

በተለይ የግብዓት ዋጋ የሚጨምረው ከትራንስፖርት ወጪ ባሻገር የወደብ ኪራይ መሆኑን አመልክተው፤ ይህ ከጊዜ አኳያ ሲታይም ትልቅ ኪሳራ የሚያስከትልና በተፈለገ ወቅት ግብዓት ለማግኘትም አስቸጋሪ እንደሚሆን አብራርተዋል።

የባሕር በር መኖር ከሥልጣኔ፣ ከአገሮችና ህዝቦች ጋር ያለውን ግንኙነትና ትስስር የሚያጠናክር መሆኑም አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል ይላሉ ዶክተር ከተማ። 

የባሕር በር ሰፊ የንግድ መሰረት በመፍጠር ምርትን በተፈለገው ጊዜና ቦታ በማቅረብ በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋል በማለት ያስረዳሉ።

የባሕር በር መኖር ተጨማሪ የሥራ እድል ይፈጥራል፣ የባሕር ምግቦችን በቀላሉ ማግኘት ያስችላል፣ ከድጋፍና ከጥገኝነት መላቀቂያ መንገድ መሆኑን መረዳት እንደሚገባም አመላክተዋል።

እንደዶክተር ከተማ ገለጻ፤ የባሕር በር እንዲኖር አሁን ላይ አጀንዳ መሆኑ ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ ነው፤ ለዚህም ሁሉም በትኩረት ሊመለከተው ይገባል።


 

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አባተ የስጋት፣ የባሕር በር ለአንድ አገር ዕድገት መሰላል ከሚባሉ መስፈርቶች መካከል የሚቀመጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህ እንደምክንያት የሚጠቅሱት በዓለም ላይ በሚካሄዱ ንግዶች በርከት ያሉ እቃዎች በአንድ ጊዜ ለማጓጓዝ  ተመራጩ የባሕር ላይ ትራንስፖርት መሆኑን ነው።  

የባሕር በር ያላቸው አገሮች ለዓለም ገበያ ክፍት ስለሚሆኑ ተመራጭነታቸውና ዕድገታቸው የተሻለ ሆኖ ይታያል ብለዋል።
በዓለም ላይ በዕድገታቸው ልቀው የሚታዩ አገሮች የባሕር በር ያላቸው ሲሆኑ፤ በዕድገታቸው ወደ ኃላ የቀሩት ደግሞ የሌላቸው መሆናቸውን ዶክተር አባተ አስረድተዋል።


 

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፐብሊክ አድምኒስትሬሽንና ዴቬሎፕመንት ማኔጅመንት መምህር ሁለመናዬ ለገሰ በበኩላቸው፤ እንደኢትዮጵያ ትልቅ የአገር ውስጥ ምርት እድገት ለሚያንቀሳቅሱ አገሮች ወደብ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የባሕር በር መኖር አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት እድገት ላይ ካለው አዎንታዊ ተጽዕኖ ባለፈ ፈርጃ ብዙ የኢኮኖሚ ትሩፋቶች እንዳሉት አመልክተዋል።

የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት ትምህርት ክፍል መምህር ደጀኔ ጣፋ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የባሕር በር ካለው የኢኮኖሚ ጠቀሜታ አኳያ የባህር በር እንዲኖር እንቅስቃሴ መጀመር ትልቅ ቁምነገር ነው።


 

አሁን ያለውን የኢኮኖሚ አቅም በእጥፍ ለማሳደግ እንዲሁም የአገሪቷን የምርታማነት ጉዞ ለማፈጠን ትልቅ ድርሻ እንዳለው አንስተዋል።

በተለይ የትራንስፖርት ወጪን መቀነስ፣ የተሳለጠ የሎጂስቲክስ ስርዓት እንዲኖር እንዲሁም በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በዓለም ላይ የኢትዮጵያን ያህል ለባህር በር ቀርቦ ወደብ አልባ የሆነ አገር እንደሌለ ገልጸው፤ በሰላማዊ መንገድ በሰጥቶ መቀበል መርህ መፍትሄ ማግኘት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት መስጠታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም