ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችላቸውን ሥምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችላቸውን ሥምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2016(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችላቸውን ሥምምነት ተፈራረሙ፡፡
ሥምምነቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላና የኮሪያ ሪፐብሊክ የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢነርጂ ሚኒስትር ሙን ኪዩ ባንግ ተፈራርመዋል።
በመርሃ ግብሩም ከመንግሥትና የግል ኩባንያዎችና ድርጅቶች የተውጣጡ የኮሪያ ሪፐብሊክ ልዑክ ቡድን አባላት የተገኙ ሲሆን ውይይትም አድርገዋል።
ስምምነቱም ሁለቱ አገራት የንግድ ልውውጥ መጠናቸውን ማሳደግ፣የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት ላይ በትብብር እንዲሰሩ የሚያስችል ነው፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ኢትዮጵያና ኮሪያ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መስርተዋል።
በተለይም እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2002 ጀምሮ የንግድ ግንኙነታቸውን ለማሳለጥ ሥምምነት መፈረማቸውን አስታውሰው፤ አገራቱ ዛሬ ያደረጉት ሥምምነት የተጀመረውን ንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል የሚያስችል ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ቡና፣አትክልትና ፍራፍሬ፣ጥራጥሬና የቅባት እህሎች እንዲሁም የስንዴ ምርትን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ላይ በሰፊው እየሰራች እንደሆነም በዚሁ ጊዜ አንስተዋል።
ኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያን ምርቶች ከሚቀበሉ አገራት መካከል ተጠቃሽ መሆኗን የተናገሩት ሚኒስትሩ ሥምምነቱ መሰል ትስሰሮች ከፍ ወዳለ ደረጃ እንደሚያሸጋግረውም አብራርተዋል።
ኮሪያ ሪፐብሊክ በቴክኖሎጂ ላይ የተሻለ ተሞክሮ ያላት በመሆኑም ሥምምነቱ በተለይም በኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በስፋት ለመስራት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
ምርቶችን ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡ የኮሪያ ሪፐብሊክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ምቹ የሥራ ቆይታ እንዲኖራቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸት ሌላው የሥምምነቱ የትኩረት ነጥብ መሆኑንም አብራርተዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በአገራቱ መካከል አሁን ያለውን የወጪ እና ገቢ ንግድ ልውውጥ ማመጣጠንም እንዲሁ ሁለቱ አገራት በቀጣይ በትብብር የሚሰሩባቸው መስኮች ናቸው።
የኮሪያ ሪፐብሊክ የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢነርጂ ሚኒስትር ሙን ኪዩ ባንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ኮሪያ ዘመናትን የሚሻገር ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
"በኮሪያ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ ሰራዊት የከፈለውን መስዋዕትነት ምንም ጊዜም አንዘነጋውም" ያሉት ሚኒስትሩ፤ በንግድና ኢንቨስትመንት በኩልም አገራቱ የተሻለ ትስስር እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ስምምነቱ ሁለቱ አገራት ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማሳደግ የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል።
ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር 1963 ላይ በይፋ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደጀመሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡