ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ባህሬን የንግድ ትብብራቸውን ለማሳደግ ተስማሙ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2016(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያና ባህሬን የንግድ ትብብራቸውን ለማሳደግ ተስማምተዋል።

በባህሬን የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀነራል ጽሕፈት ቤት አምባሳደር ሽፈራው ገነቴ ከባህሬን ግብርና እና ማዘጋጃ ቤት ሚኒስትር ኢንጂነር ዋኢል ቢን ናስር አል ሙባረክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም የኢትዮጵያን የግብርናና የእንስሳት ውጤቶች ወደ ባህሬን ገበያ መላክ በሚቻልበትና የሀገራቱን የንግድ ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታዎች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።

በተጨማሪም በአዲስ አበባና በማናማ ከተሞች መካከል የንግድና የቱሪዝም ትስስር መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ውይይት አድርገዋል።

አምባሳደር ሽፈራው ኢትዮጵያ ከቡና ባሻገር የቅባት እህሎች፣የሆርቲ ካልቸር፣ቅመማ ቅመም እና ሌሎች የግብርና ውጤቶች መገኛ መሆኗን ለሚኒስትሩ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የተለያዩ የግብርናና የእንስሳት ውጤቶችን፣ ቅመማ ቅመሞችንና ሌሎች ምርቶችን ወደ አውሮፓ እና መካከለኛው ምስራቅ እየላከች እንደምትገኝም አምባሳደሩ አብራርተዋል።

የባህሬን ግብርና እና ማዘጋጃ ቤት ሚኒስትር ኢንጂነር ዋኢል ቢን ናስር አል ሙባረክ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ባህሬን የዓለም አቀፉ የእንስሳት ጤና ድርጅት አባል መሆናቸውን በማስታወስ የኢትዮጵያን ምርቶች በባህሬን ለማስተዋወቅ ፍላጎት እንዳለ ገልጸዋል።

ለዚህም የኢትዮጵያን የግብርና ምርቶች ለማስተዋወቅ የተለያዩ መድረኮችንና አውደ ጥናቶችን የማዘጋጀት ፍላጎት መኖሩን መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስነብቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም