ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ሥራ አበረታች መሆኑ ተገለጸ

ሐረር፤ ጥቅምት 9/2016 (ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ሥራ አበረታች መሆኑን የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤይ.ዲ) የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስተር ስኮት ሆክላንድ ገለጹ። 

በዳይሬክተሩ የተመራ ልዑክ በሐረሪ ክልል የጤና መድህን አገልግሎትና ጤና ተቋማት የውስጥ ገቢን ለማሳደግ እያከናወኗቸው ያሉ ሥራዎችን ዛሬ ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ወቅት ሚስተር ስኮት እንደገለጹት፣ የክልሉ ጤና ቢሮ ህብረተሰቡ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አባል ሆኖ ያለችግር የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ እያከናወነ ያለው ሥራ አበረታች እንደሆነ መመልከታቸውን ገልጸዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አባል የሆኑ ዜጎች በአነስተኛ የገንዘብ መጠን በጤና ተቋማት የጤና አገልግሎት ሲያገኙ መመልከታቸውንም ተናግረዋል።

ሚስተር ስኮት አክለው እንዳሉት በክልሉ የሚገኙ ጤና ተቋማት የውስጥ ገቢን በማሳደግ የጤና ተደራሽነትን ለማጎልበት እያከናወኑት ያለው ሥራም የሚበረታታ ነው።

ዩ.ኤስ.አይ.ዲም የክልሉን የጤና አገልግሎት ለማጠናከር የተለያዩ የቴክኒካል፣ የአቅም ግንባታ እና ሌሎች ድጋፎችን ማድረጉን ጠቁመው፣ በቀጣይም የድጋፍ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።


 

የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ያሲን አብዱላሂ በበኩላቸው የልዑክ ቡድኑ ጉብኝት በክልሉ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ያለበትን ደረጃ ለመመልከት ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በክልሉ ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አባል መሆኑን ተከትሎ የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ በተሰሩ ስራዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡንም ገልጸዋል።

ለእዚህም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አባል የሆኑ 110 ሺህ ሰዎች በ2015 በጀት ዓመት የጤና አገልግሎት ማግኘታቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በተለይ ቢሮው በጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር ሲያነሱት የነበረውን ችግር ለመፍታት 9 የማህበረሰብ መድሀኒት ቤቶችን በመክፈትና የህክምና ግብዓት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን የመሙላት ሥራ በትኩረት ማከናወኑን አስረድተዋል። 

በዚህም በክልሉ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ላይ የሚከናወኑ ሥራዎች አበረታች ውጤት እየተገኘባቸው መሆኑን ነው አቶ ያሲን ያመለከቱት።

በተለይ ባለፉት ዓመታት ዩ.ኤስ.አይ.ዲ በክልሉ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ላይ እየተከናወነ የሚገኘውን ሥራ ለማጠናከር የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ እንደነበር አንስተው፣ በቀጣይም የድጋፍ ሥራው እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

 

   

 

 

 

 
 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም