የኢፌዴሪ አየር ኃይል በዘመናዊ ትጥቅና ብቁ የሰው ኃይል በመታገዝ ለኢትዮጵያ አየር ክልል አስተማማኝ ዘብ ሆኖ ተገንብቷል - ኢዜአ አማርኛ
የኢፌዴሪ አየር ኃይል በዘመናዊ ትጥቅና ብቁ የሰው ኃይል በመታገዝ ለኢትዮጵያ አየር ክልል አስተማማኝ ዘብ ሆኖ ተገንብቷል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2016(ኢዜአ)፡- የኢፌዴሪ አየር ኃይል በዘመናዊ ትጥቅና ብቁ የሰው ኃይል በመታገዝ ከመቼውም ጊዜ በላይ የኢትዮጵያ አየር ክልል አስተማማኝ ዘብ ሆኖ ተገንብቷል፡፡
አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአየር ኃይሉን ግዳጅ የመፈጸም አቅም ከፍ ለማድረግ የተከናወኑ ስራዎች በተጨባጭ ለውጥ ማምጣታቸውም ተገልጿል፡፡
የኢፌዴሪ አየር ኃይል የአየር መከላከያ መሳሪያዎች ጥገና መምሪያ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዳሉት፤ አሁን ላይ አየር ኃይሉ የማድረግ አቅም ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍ ብሏል፡፡
የአየር መከላከያ መሳሪያዎች ጥገና መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ተሾመ ባጫ፤ አየር ኃይሉን በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና በሰለጠና የሰው ኃይል በማደራጀት ረገድ አበረታች ስራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ቀን ከሌት የኢትዮጵያን አየር ክልል በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ የሚያስችል አየር ኃይል መገንባት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በማዕከል እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችም የአየር ኃይሉን ዝግጁነት ከፍ የሚያደርጉ ስለመሆናቸውም ነው የጠቆሙት፡፡
የወቅቱን ቴክኖሎጂ መሰረት በማድረግ በየጊዜው ከቴክኖሎጂው ጋር የሚሄዱ የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
አየር ኃይሉ የታጠቃቸውን መሳሪያዎች በመጠገን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ የሚያስችል ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት መቻሉንም እንዲሁ፡፡
በኢፌዴሪ አየር ኃይል የራዳር ጥገና ባለሙያ ሲቲክ ምትኩ ፈንታ በበኩላቸው አየር ኃይሉ ዘመኑን የሚመጥኑ ራዳሮችን በመጠቀም የኢትዮጵያን አየር ክልል በአስተማማኝ ሁኔታ እየጠበቀ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በተለይም ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ረገድ እጅግ አመርቂ ስራ ተከናውኗል ነው ያሉት፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች ራዳሮችን በአገር ውስጥ አቅም መገንባት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡