የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ወቅታዊና እያደገ የመጣውን የሎጂስቲክስ አቅም ታሳቢ ያደረገ ነው--አቶ አብዱልበር ሸምሱ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ወቅታዊና እያደገ የመጣውን የሎጂስቲክስ አቅም ታሳቢ ያደረገ ነው--አቶ አብዱልበር ሸምሱ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ወቅታዊና እያደገ የመጣውን የሎጂስቲክስ አቅም ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አብዱልበር ሸምሱ ገለጹ።
የባህር ትራንስፖርት ለዓለም ንግድ እንቅስቃሴ እንደ ጀርባ አጥንት የሚታይ በዓለም ረዥም ታሪክ ያለው ዘርፍ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ የባህር በር ማግኘት ብቻውን የአንድ አገር ጥቅል የምርት እድገትን ከ25 እስከ 30 በመቶ ከፍ እንደሚያደርገው የተባበሩት መንግስታት ጥናትን ጠቅሰው ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የወጭና ገቢ ንግዷን በጅቡቲ በኩል የምታከናውነው ኢትዮጵያም የባህር በር በማጣቷ ምክንያት በዓመት 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ለወደብ ኪራይ ታወጣለች፡፡
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አብዱልበር ሸምሱ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ 9 ሁለገብ እና 2 ነዳጅ ጫኝ መርከቦች የአገሪቷን የገቢና ወጪ ንግድ ለማሳለጥ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ይሁን እንጂ የባህር በር አለመኖሩ በሎጂስቲክስ ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ነው ያስረዱት፡፡
የባህር በር አለመኖር በተለይ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው እንደ ፍራፍሬ ያሉ ቶሎ የሚበላሹ ምርቶችን ጥራታቸውን ጠብቆ በፍጥነት ተደራሽ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ መሆኑንም ነው የሚናገሩት፡፡
ይህም በተወዳዳሪነት ላይ የራሱን እክል በመፍጠር ወጪ ንግዱ እንዲቀንስ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም እቃዎች በሚገቡና በሚወጡበት ወቅት በወደብ የሚኖራቸው ቆይታ ከፍተኛ ወጭ እንዳለው አመላክተዋል።
ይህም የዋጋ ንረት እንዲከሰት እንደሚያደርግም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቸኛ በሚባል ደረጃ የንግድ መርከቦች ያሏት አገር በመሆኗ የባህር በር ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት እውን ማድረግ ከተቻለ ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም እንደሚፈጠር አብራርተዋል።
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የሎጂስቲክ ወጭን በማቃለል የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ካላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ አንጻር የባህር በር መኖሩ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለውም ጠቅሰዋል።
ይህም የሎጂስቲክስ ዘርፍ ከማሳለጥ ባሻገር ኢኮኖሚውን በማነቃቃት ለስራ እድል ፈጠራ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።