ቀጥታ፡

የእንስሳት ጤናና ደህንነት አዋጅ በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ትግበራ ይገባል - የግብርና ሚኒስቴር 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2016(ኢዜአ)፦ የእንስሳት ጤናና ደህንነት አዋጅ በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ትግበራ የሚገባ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ዓለም አቀፉ የእንስሳት ቀን በኢትዮጵያ ለ13ኛ ጊዜ በዓለም ደግሞ ለ97ኛ ጊዜ ተከብሯል።     

የግብርና ሚኒስቴርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ሕክምናና ግብርና ኮሌጅ ቀኑን በተለያዩ መርሃ ግብሮች በቢሾፍቱ ከተማ አክብረዋል።

የግብርና ሚኒስቴር  የእንስሳት ጤናና ቬተርነሪ ፐብሊክ ሄልዝ መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ውብእሸት ዘውዴ፤ ኢትዮጵያ ባላት የእንስሳት ሀብት በአፍሪካና በዓለም በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ አገራት መካከል አንዷ ብትሆንም እስካሁን በሚፈለገው መጠን መጠቀም አልቻለችም ብለዋል።  

ለእንስሳት በቂ እንክብካቤ፣ የምግብ፣ መጠለያ እንዲሁም የጤና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ላይ ክፍተቶች መኖራቸውንና ይህም በምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ጠቅሰዋል።
 

በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል የእንስሳት ጤናና ደህንነት አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።

አዋጁ በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ትግበራ የሚገባ መሆኑንም ነው የተናገሩት። 

የኢትዮጵያ እንስሳት የወጭ ንግድ በሚፈለገው ደረጃ እየተጓዘ አይደለም ያሉት ዶክተር ውብእሸት የአዋጁ ስራ ላይ መዋል መሰል ችግሮችን ለመፍታት እንደሚረዳ አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ሕክምናና ግብርና ኮሌጅ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር አሶሺዬት ዲን ዶክተር ፉፋ አቡና፤ የእንስሳት ጤና የማስጠበቁ ጉዳይ ከሰው ሕይወትም ጋር የሚገናኝ በመሆኑ የባለድርሻ አካላት ልዩ ትኩረት እንደሚሻ አስገንዝበዋል።

 

     

 

 

 

         

 

 

 

 

 

 

 

  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም