ቀጥታ፡

የመከላከያ ሰራዊት የሪፎርም ስራ በሁሉም መስክ የላቀ ውጤት እየተመዘገበበት ነው- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2016 (ኢዜአ)፦ የመከላከያ ሰራዊት የሪፎርም ስራ በሁሉም መስክ የላቀ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ የመከላከያ ሎጅስቲክስ ዋና መምሪያ የዝግጁነት አቅምና የሥራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።

በዚሁ ወቅት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ በኢትዮጵያ የትጥቅ ዝግጁነትና ዘመናዊ ጦር የማቋቋም ስራ በሂደት ቀጥሎ ዛሬ ላይ በእጅጉ መዘመኑን ገልጸዋል። 

በመሆኑም ከዛሬ 116 ዓመት በፊት ዘመናዊ ሰራዊት ለማቋቋም የተደረገውን ጥረት መነሻ በማድረግ የሰራዊት ቀን መከበር መጀመሩን አንስተው ዘንድሮም በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል ብለዋል። 

የኢትዮጵያንና የሰራዊቱን ታሪክ በማጥናት የሰራዊቱ ቀን ታሪኩን በሚመጥን መልኩ በድምቀት የሚከበር መሆኑን ገልጸዋል። 

በመከላከያ ሎጅስቲክስ መምሪያ የተሰሩ ፈጠራና የዝግጁነት ሥራዎችም የሰራዊቱን አቅም የሚያጎለብቱና ለሰራዊቱ ቀን ልዩ ድምቀት የሚሰጡ ናቸው ብለዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት የአገር መከላከያ ሰራዊትን አቅም ማጎልበት ያስቻለ ተቋማዊ የለውጥ ስራ ተከናውኖ የላቀ ውጤት መመዝገቡንም አንስተዋል።

የአየር ኃይል፣ ሎጅስቲክስ መምሪያ፣ መከላከያ ኢንዱስትሪና መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ሪፎርሙን ተከትሎ እምርታዊ ለውጥ አምጥተዋል ብለዋል።

በመሆኑም አሁን ላይ በአስተማማኝ መልኩ ግዳጅ መፈፀም የሚችል ዘመናዊና የሀገር አለኝታ የሆነ ሰራዊት ተገንብቷል ብለዋል።

የመከላከያ ሎጅስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል አብዱራህማን እስማኤል፣ የሰራዊቱን የግዳጅ አፈፃጸም ውጤታማነት የማስቀጠል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የሰራዊቱን ሁለንተናዊ ዝግጅነት ይበልጥ ለማሳደግም የፈጠራ፣ የማሻሻያና የማደስ ሥራ በመስራት ሃብትን በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ እንዲውል እየተደረገ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎችን በማስፋት የተቋሙን አቅም መገንባት የሚያስችሉ ስራዎችን በማከናወን የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።

የመከላከያ ሎጅስቲክስ መምሪያ የጥገናና የፈጠራ ሙያተኞች የተሰጣቸው ዕውቅና ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል። 

በመከላከያ ሎጅስቲክስ መምሪያ የጥገና ሙያተኛ ሻለቃ ተሾመ አማከለው፤ በኦራል ተሽከርካሪ ላይ በሰሩት የፈጠራ ስራ የተቸራቸው ዕውቅና ለቀጣይ ስራ የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በመከላከያ ሎጅስቲክስ መምሪያ በጥገና መምሪያ የሮኬትና ሚሳኤል ዴስክ አስተባባሪ ሌተናል ኮሎኔል ትዝታ ታደሰ፤ ተጥለው የነበሩ መሳሪያዎችን በፈጠራ ስራ በማስደገፍ የተሰሩት ስራዎች የሰራዊቱን የውጊያ አቅም የሚያጎለብቱ ናቸው ብለዋል።


 

በመከላከያ ሎጅስቲክስ መምሪያ የከባድ ተሽከርካሪ አውቶሞቲቭ መሃንዲስ ሃምሳ አለቃ ዳዊት ዘበነ፤ በተሰጣቸው እውቅና መደሰታቸውን ገልጸው፣ ሽልማቱ የሁላችንም ነው ብለዋል። 


 

በጉብኝቱም የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ዲኤታ ማርታ ሉዊጂ፣የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፣ የሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖችና ሌሎች እንግዶች በቢሾፍቱ የሚገኘውን የመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ የዝግጁነት አቅምና የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።

በዕለቱም የመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ ያለማው የስንዴ ሰብል፣ የመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ የዝግጁነት ወርክ ሾፕ ማዕከል፣ የመካከለኛና የከፍተኛ ከባድ መሳሪያ የፈጠራ፣ የማሻሻያና የጥገና ሥራዎች ተጎብኝተዋል። 

የመከላከያ ሰራዊት ቀን ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም ለ116ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ይሆናል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም