ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላና እውቅና ያለው ስርዓተ ትምህርት እንድትተገብር  በቅንጅት እንደሚሰራ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላና እውቅና ያለው ስርዓተ ትምህርት እንድትተገብር  በቅንጅት እንደሚሰሩ  የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩትና ትምህርት ሚኒስቴር ገለጹ።

የደረጃዎችና የጥራትን ጉዳይ በሁሉም የትምህርት እርከኖች ላይ በስርዓተ ትምህርት ውስጥ አካትቶ ማስተማር እንደሚገባም ተጠቁሟል።

የዓለም የደረጃዎች ቀን “የጋራ ራዕይ ለተሻለ ዓለም” በሚል መሪ ቃል ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ደረጃዎች ለትምህርት ሥርዓቱ፣ ለምርምርና ስርጸት በሚኖራቸው ፋይዳ ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከጥናትና ምርምር ተቋማት ጋር ዛሬ የምክክር መድረክ አካሂዷል።


 

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሠረት በቀለ እንደገለጹት፤ ደረጃዎችና ጥራት በስርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ጥረት ሲደረግ ቢቆይም እስካሁን ወደ ተግባር አልተገባም።

ከ17ቱ የዘላቂ የልማት ግቦች አንዱ ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ መሆኑን በማንሳት፤ ከዚህ አኳያ በሀገሪቱ የሚሰጠው ትምህርት  ውስንነት ይታይበታል ብለዋል።

በመሆኑም ዘርፉ ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲኖረው በማድረግ ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ ከትምህርት ሚነስቴር ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በሁሉም የትምህርት እርከኖችም የደረጃዎችና የጥራትን ጉዳይ በስርዓተ ትምህርት በማካተት ማስተማር እንደሚገባ ነው የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሯ።


 

የትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሰለሞን ቢኖር በበኩላቸው፤ የትምህርት ፕሮግራሞችና የሥርዓተ ትምህርት ደረጃዎችን ለማሻሻል ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመተባበር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተደራሽነት ላይ የተሻለ ስኬት ቢኖራትም የሚተገበሩ ስርዓተ ትምህርቶችና መሰረተ ልማቶች ከዓለም አቀፍ መስፈርት አንጻር ብዙ የቤት ስራ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

ለአብነትም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ማደሪያ፣ የመምህራን ቢሮ፣ የመማሪያ ክፍሎች ደረጃቸውን የጠበቁ አለመሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር ደረጃዎችን በሥርዓተ ትምህርቱ ከማካተት ባሻገር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ወርክሾፖችን፣ የላቦራቶሪ ደረጃዎችን ለማሳደግ ከኢንስቲትዩቱ ጋር እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲዎችና በምርምር ተቋማት የሚወጡ ምርምሮች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ከኢንስቲትዩቱ ጋር በጋራ እንደሚሰሩ አመላክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም