የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ ሕግን የተከተለና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ነው - ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተንታኝ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ ሕግን የተከተለና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ነው - ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተንታኝ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ ሕግን የተከተለና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ መሆኑን አንድ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተንታኝ ገለጹ።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1982 በጃማይካ በተፈረመው የዓለም የባሕር ሕግ ስምምነት መሠረት የባሕር በር የሌላቸው አገራት ወደብ የመጠቀም እንዲሁም በባሕር ውስጥ የሚገኙ ኃብቶችን የመጠቀም መብት አላቸው።
ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ተገቢና ዓለም አቀፍ መርህንም የተከተለ መሆኑ ይታወቃል።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ ከባሕር በርና አማራጭ ወደቦች ጋር በተያያዘ ያነሱት ሃሳብም የሰጥቶ መቀበል መርህን የተከተለና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።
የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት አትክልት አጥናፉ፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ ሕግን የተከተለና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
የባሕር በር ካላቸው አገራት ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት በማድረግ ጥያቄዋን በማቅረብና በመደራደር የመጠቀም መብት ያላት መሆኑን አስረግጠዋል።
በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ የዲፕሎማሲ አካሄድን በመከተል ቀጣናዊ ትስስርን መፍጠር የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በተለይም ከአፍሪካ ቀንድ ቀጣና አገራት ጋር በትብብርና በሰጥቶ መቀበል መርህ በመሥራት የሕዝቦችን ተጠቃሚነትና የምጣኔ ኃብት እድገት ማሳለጥ ይገባታልም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ መገንባት ከራስ አልፎ የጎረቤት አገራትን አብሮ የመልማትና የጋራ ተጠቃሚነት መሠረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ አገራት በሁሉም መስክ ትብብርና ትስስር በመፍጠር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
የባሕር በርም ዓለም አቀፍ ሕጎችን፣ የጋራ ተጠቃሚነትንና አብሮ መልማትን መሠረት ያደረገ የአጠቃቀም መርህን የሚከተል መሆኑን አብራርተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1952 ባሳለፈው የውሳኔ ሃሳብ ቁጥር 390/5 መሠረት የባሕር በር ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።