ዩኒቨርሲቲዎች ሙያዊ ነጻነታቸው ተጠብቆ ተልዕኳቸውን በአግባቡ መወጣት የሚችሉት ራስ ገዝ ሲሆኑ ነው -ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲዎች ሙያዊ ነጻነታቸው ተጠብቆ ተልዕኳቸውን በአግባቡ መወጣት የሚችሉት ራስ ገዝ ሲሆኑ ነው -ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
አዲስ አበባ ፤ጥቅምት 8/2016(ኢዜአ)፦ ዩኒቨርሲቲዎች ሙያዊ ነጻነታቸው ተጠብቆ ተልዕኳቸውን በአግባቡ መወጣት የሚችሉት ወደ ራስ ገዝነት ሲሸጋገሩ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ይህን ያሉት የተቋማቸውን የ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ነው።
የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1294/2015 ግንቦት 17 ቀን 2015 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁ ይታወቃል።
በአዋጁ መሰረት ዩኒቨርሰቲዎች ራስ ገዝ መሆናቸው በራሳቸው ገቢ ከማመንጨት ባለፈ ስርዓተ ትምህርቱን በራሳቸው መንገድ በነጻነት በመቅረጽ ጥራት ያለው ትምህርት መስጠት የሚችሉበትን እድል ይፈጥራል።
በአዋጁ መሰረት ራስ ገዝነት የራሳቸውን የአስተዳደር መዋቅር፣ የሰው ኃይል ምደባ፣ ቅጥር እና የደመወዝ ውሳኔን በነጻነት እንዲያዘጋጁ አስተዳደራዊ ነጻነት እና ሥልጣንን ይሰጣል።
በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል የመጀመሪያው ራስ ገዝ ሆኖ ተቋቁሟል።
በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በዩኒቨርሲቲው ተከማችተው የነበሩ ችግሮችን በማጥራት ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲወጣ የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚሰሩም ነው የተናገሩት።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተልዕኳቸውን በአግባቡ ሊወጡ የሚችሉት በእውቀትና ምርምር ላይ ተመርኩዘው በነጻነት ሲሰሩ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ ለዚህ ደግሞ በተለይም ተቋማቱን ከፖለቲካ ጥገኝነት ማላቀቅ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ዩኒቨርስቲዎችን ሙያዊ ነጻነታቸው ተጠብቆ ተልዕኳቸውን በአግባቡ የሚወጡት ወደ ራስ ገዝነት ሲሸጋገሩ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ሁሉም የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ጊዜያቸውን ጠብቀው ራስ ገዝ እንደሚሆኑ የጠቀሱት ፕሮፌሰሩ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርስቲዎችን ራስ ገዝ እናደርጋለን ብለዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የነበረውን ስር የሰደደ ችግር ደረጃ በደረጃ እየፈቱ በመሄድ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።