ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን አስተማማኝና ዘመናዊ አየር ሃይል የመገንባት ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2016(ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያ አየር ሃይልን በሁሉም መስክ የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን አስተማማኝና ዘመናዊ አየር ሃይል የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በተለይም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ አየር ኃይሉ በሁሉም ረገድ በመዘመንና ስኬታማ በመሆን ሀገር የምትኮራበት ታላቅ ተቋም መሆኑንም ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ አየር ኃይል አሁን ላይ በውጊያ መሠረተ-ልማት፣ በሰው ኃይል ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራና አጠቃቀም በአጭር ጊዜ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገቡን በተቋሙ የተለያዩ ዲፓርትመንት ኃላፊዎች ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል አስተማማኝ የሀገር መከታ በመሆን ለየትኛውም ግዳጅ አፈጻጸም ብቁና ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ አየር ኃይልን በሁሉም መስክ የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን ዘመናዊ ተቋም የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።


 

በአየር ኃይል አቪዬሽን ከባድ ጥገና ማዕከል የሮተሪ ዲፓርትመንት ዊንግ መምሪያ ኃላፊ  ሌተናል ኮሎኔል ኢንጂነር ሙሉቀን ደርሶ፤ አየር ኃይሉ የኢትዮጵያን ታላቅነት በሚመጥን መልኩ በሁሉም መስክ በዘመናዊ መልኩ እየተገነባ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በአየር ኃይሉ ለውጊያ፣ መለማመጃና ለትራንስፖርት አገልግሎት የሚውሉ አውሮፕላኖችን አስተማማኝ እድሳትና ጥገና በማድረግ ላይ ስለመሆኑም አንስተዋል።

በአየር ኃይሉ ቀደም ሲል የነበሩ አውሮፕላኖችን ከአናሎግ ወደ ዲጂታል የማሻሻያ ሥራ በማከናወን የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

የአየር ኃይል የከባድ ጥገና ማዕከል የምርምር እና ልማት ክፍል ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ወንድማገኝ አርዓያ፤ በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በማሻሻያ ሥራዎች ስኬታማ መሆኑን ገልፀዋል። 

በከባድ የጥገና ማዕከል አውሮፕላኖችን የማዘመን፣ የዕይታና ዒላማ አቅማቸውን የማጎልበት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም አየር ኃይሉ ያወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት መቻሉን ገልጸው፤ በቀጣይም ተጨማሪ ገቢዎችን ለማስገኘት እንሰራለን ብለዋል፡፡

በአየር ኃይል የአቪዬሽን ጥገና ማዕከል መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ደረጄ አስታጥቄ፤ አየር ኃይል የውጊያ መሠረተ-ልማቶችን በመገንባት ያከናወናቸው ተግባራት ግዳጆችን በአስተማማኝ ብቃት መወጣት የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡    

በአየር ኃይሉ የትራንስፖርት ሄሊኮፕተር ጥገና ስኳድሮን ኃላፊ ሻለቃ አንድነት ብርሃኑ በበኩላቸው፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአየር ኃይሉ በርካታ አመርቂ ሥራዎች ስለመከናወናቸው አብራርተዋል።


 

በአየር ኃይሉ የሄሊኮፕተር አብራሪዎቹ ሌተናል ኮሎኔል አየለ ዳዊት እና ሻለቃ ፀጋዬ አሰፋ ፤ አየር ኃይሉ አሁን ላይ በቴክኖሎጂ አጠቃቀምም ይሁን በግዳጅ አፈጻጸም አስተማማኝ ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል።

በአስቸኳይ ተልዕኮና ግዳጅ በቀንም ይሁን በሌሊት በመብረር ያሰብነውን ማሳካት የሚያስችል ቁመና ላይ እንገኛለንም ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም