የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ''ዲቢኢ ተዐውን'' የተሰኘ ከወለድ ነጻ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ አገልግሎት በይፋ አስጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ''ዲቢኢ ተዐውን'' የተሰኘ ከወለድ ነጻ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ አገልግሎት በይፋ አስጀመረ
አዲስ አበባ ፤ጥቅምት 8/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ''ዲቢኢ ተዐውን'' የተሰኘ ከወለድ ነጻ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ አገልግሎት በይፋ አስጀመረ።
የባንኩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ ከወለድ ነጻ የሆነ የባንክ አገልግሎት ጠቀሜታው የላቀ ነው።
ሆኖም ላለፉት ዓመታት ሳይተገበር መቆየቱ አልሚዎች በሚፈልጉት የፋይናንስ አማራጭ እንዳይሰማሩ ማድረጉን አንስተዋል።
በዚህም ከዘርፉ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አነስተኛ አድርጎት መቆየቱን ነው የተናገሩት።
ዛሬ በይፋ የተጀመረው "ዲቢኢ ተዐውን" ከወለድ ነጻ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ አገልግሎት ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ለሚፈልጉ አልሚዎች የተዘጋጀ አማራጭ መሆኑን አብራርተዋል።
በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በኮንስትራክሽን ግብዓቶች ምርትና በአስጎብኚ አገልግሎት ለሚሰሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።
አገልግሎቱ ከሸሪዓ ህግ ጋር ተጣጥሞ እንዲሰጥ በዘርፉ እውቀት ያላቸው አማካሪዎችና የሃይማኖት አባቶች ከባንኩ ጋር የሚሰሩበት አግባብ መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም "ዲቢኢ ተዐውን" ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት በዋናው መስሪያ ቤትና በሁሉም የባንኩ ቅርንጫፎች ከዛሬ ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ አብዱልከሪም በድረዲን በበኩላቸው፤ ዲቢኢ ተዐውን መጀመሩ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች መሳተፍ ለሚሹ ሙስሊም የህብረተሰብ ክፍሎች አስደሳች ስራ ነው ብለዋል።
በመሆኑም በሸሪዓ ህግ መሰረት በተዘጋጀው የፋይናንስ አገልግሎት በመጠቀም በአገሪቱ የልማት ስራዎች ላይ ተሳትፎን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ዛሬ በይፋ የተጀመረው ከወለድ ነጻ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ አገልግሎት በኢኮኖሚው ውስጥ ፍትሐዊነትንና አካታችነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።
የፋይናንስ አገልግሎቱ በፍትሐዊነት ተደራሽ መሆኑ ለሀገሪቱ እድገት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
መንግስት የኢኮኖሚ ልማት ስራዎች ጤናማ እድገት እንዲኖራቸውና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እኩል ተጠቃሚ እንዲያደርጉ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።