ለግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ከዘርፉ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ ነው-የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ለግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ከዘርፉ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ ነው-የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 8/2016 (ኢዜአ) ፦ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ከዘርፉ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በተመረጡ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ በግብርና እና በግብርና ማቀነባበሪያ ላይ በጋራ ከሚሰሩ አጋር አካላት ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ ውይይት አድርጓል።
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ እንዳሉት፤ ለግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ዓለም አቀፍ ልምድ ካላቸው ባለድርሻዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ለዘርፉ ስርዓተ-ትምህርት በማዘጋጀትና የተግባር ትምህርት ቁሳቁስ በማሟላት በተመረጡ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ሰልጣኞች በግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ትምህርታዊ የተግባር ልምምድ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
የክህሎት ልማት ስራ ረጅም ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፕሮጀክት ድጋፍ አስተባባሪ አያልነህ አባዋ በበኩላቸው፤ ለኢንዱስትሪዎች መሰረተ ልማት የማሟላት፣ የሰው ኃይል ማብቃትና ከአርሶ አደሮች ጋር የማስተሳሰር ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ ለዘርፉ ስድስት ሺህ የሰው ኃይል ለማሰልጠን እቅድ መያዙንም ጠቁመዋል።