ቀጥታ፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያን የዝግጁነት አቅምና የሥራ እንቅስቃሴን ጎበኙ

አዲስ አበባ ፤ጥቅምት 8/2016(ኢዜአ)፦ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ የዝግጁነት አቅምና የሥራ እንቅስቃሴን ጎበኙ።

በፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በተመራው ጉብኝት የመከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮችና የሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች ተሳትፈዋል። 

የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሠ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ዲኤታ ማርታ ሉዊጂ፣ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፣ የመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አብዱራህማን እስማኤል እና ሌሎችም ተገኝተው በቢሾፍቱ የሚገኘውን የመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ የዝግጁነት አቅምና የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።


 

በጉብኝታቸውም የመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ ያከናወናቸው ውጤታማ የፈጠራ ሥራዎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

የመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ ያለማው የስንዴ ሰብል፣ የመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ የዝግጁነት ወርክ ሾፕ ማዕከል፣ የመካከለኛና የከፍተኛ ከባድ መሳሪያ የፈጠራ ሥራዎች ተጎብኝተዋል። 

በመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ የሥራ እንቅስቃሴ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ መሃንዲሶችና ሙያተኞችም በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ዕውቅና እና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። 


 

የመካላከያ ሰራዊት ቀን ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም ለ116ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም