ቀጥታ፡

የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማበረታታት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው- የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2016(ኢዜአ)፦የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማበረታታት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ።

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ አዳዲስ ተመራቂ ዜጎችና ቀጣሪ ድርጅቶች የሚገናኙበት አገር አቀፍ የሥራ አውደ-ርዕይ በሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቷል።

የሥራ አውደ-ርዕዩን መርቀው የከፈቱት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን፤ የዜጎችን የሥራ አጥነት ችግር በመቀነስ ሁለንተናዊ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋት መንግሥት እያደረገ ካለው ጥረት ጎን ለጎንም የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

በየዓመቱ በአማካይ ለ3 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በ2030 ከ20 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የፋይናንስ ተደራሽነት ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ አሠራሮችን በመዘርጋት የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማበረታታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል። 

የአፍሪካ ጆብስ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮሱፍ ረጃ፤ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚቆየው የሥራ አውደ-ርዕይ ከ6 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚያገኙበት እንደሚሆን ገልፀዋል።


 

በአውደ-ርዕዩ ላይ ከ200 በላይ ሥራ ቀጣሪ ድርጅቶች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ በመጠቆም፤ በቀጣይም ለዜጎች የሥራ ዕድል ፍላጎት አጋዥ የሚሆኑ የሥራ አውደ-ርዕዮችን እናዘጋጃለን ብለዋል።

የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሳሙኤል ያለው፤ ድርጅታቸው የሥራ ዕድል ከመፍጠር በተጨማሪ የተቋማት አቅም ግንባታ ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በቴክኖሎጂና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ የወጣቶችን አቅም ለማሳደግ ከሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ትምህርትና ሥልጠና መሰጠቱንም ገልፀዋል።


 

በአውደ-ርዕዩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ሥራ ቀጣሪ ድርጅቶችም አገር አቀፉ የሥራ አውደ-ርዕይ አሰሪና ሠራተኛን በአንድ ማዕከል በማገናኘት ለሥራ ዕድል ፈጠራው ከፍተኛ እገዛ እንዳለው ገልፀዋል።

በአውደ-ርዕዩ ላይ የተገኙት ሥራ ፈላጊዎችም ሁነቱ መልካም አጋጣሚ የፈጠረላቸው መሆኑን ተናግረዋል። 

በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የተከፈተውን የሥራ አውደ-ርዕይ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የደረጃ ዶት ኮም እና በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የጋራ ትብብር የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም