ቀጥታ፡

የተሽከርካሪዎች ከተፈቀደላቸው ክብደት በላይ መጫን መንገዶችን ለከፍተኛ ብልሽት እየዳረገ ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2016(ኢዜአ)፦  የተሽከርካሪዎች ከተፈቀደላቸው ክብደት በላይ መጫን መንገዶችን ለከፍተኛ ብልሽት እየዳረገ መሆኑ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በሞጆ የተሽከርካሪ ክብደትና መቆጣጠሪያ ጣቢያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርኃ-ግብር አካሂዷል። 

የሞጆ የተሽከርካሪ ክብደትና መቆጣጠሪያ ጣቢያ ኃላፊ ያሬድ አለማየሁ፤ ከተፈቀደላቸው የመጫን አቅም በላይ የሚጭኑ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር በአገሪቱ ዋና ዋና መንገዶች ላይ 14 የክብደትና መጠን መቆጣጠሪያ ሚዛን ጣቢያዎች እንዳሉ ገልፀዋል።

በጣቢያው በቀን ከ80 እስከ 120 ለሚሆኑ ተሽከርካሪዎች የክብደት መጠን እንደሚለካ ገልፀው፤ በዚህም 40 በመቶ የሚሆኑት አሽከርካሪዎች ከተፈቀደው ክብደት በላይ እንደሚጭኑ ተናግረዋል።

በመሆኑም ከተፈቀደላቸው ክብደት በላይ የተሽከርካሪዎች መጫን በተለይም መንገዶችን ለከፍተኛ ብልሽት እየዳረገ መሆኑን አብራርተዋል።

ከተቀመጠው የተሽከርካሪዎች የመጫን አቅም በላይ ሲጭኑ በሰውና በንብረት እንዲሁም በሀገር ኢኮኖሚ  ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑንም አንስተዋል።

በመሆኑም አሽከርካሪዎች መንገድ "የእኔ ነው" በሚል በሕግ በተደነገገው የክብደት መጠን መጫን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ኢዜአ ካነጋገራቸው አሽከርካሪዎች መካከል ሳምሶን ታደሰ፣  ሳሙኤል ጌታቸው እና ብርሃን ፀጋዬ፤ ሕግን ተከትሎ ማሽከርከር የራስና የቤተሰብን ሕይወት መጠበቅና ሀገርንም ከጉዳት መታደግ  በመሆኑ  ሁላችንም በዚሁ መሠረት መሥራት አለብን ብለዋል። 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም