የኢትዮጵያ የባህር በርና አማራጭ ወደቦችን የመጠቀም ሃሳብ ከአገራት ጋር በትብብር የመልማት መርህን የተከተለ ነው- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በርና አማራጭ ወደቦችን የመጠቀም ሃሳብ ከአገራት ጋር በትብብር የመልማት መርህን የተከተለ ነው- ምሁራን
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በርና አማራጭ ወደቦች ተጠቃሚነት ጉዳይ በቀጣናው ያሉ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅና ከአገራት ጋር በትብብር የመልማት መርህን የተከተለ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሕግና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን ገለጹ።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ከምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ጋር የተቆራኘ መሆኑንም ምሁራኑ ጠቅሰዋል።
የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ኮሌጅ ዲንና የሕግ፣ የሰላምና ልማት ምሁር ዶክተር ሮባ ጴጥሮስ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ የባህር በር የሌላቸው አገራት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፎች መኖራቸውን አብራርተዋል።
ከዚህ አኳያም የኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚነት ጥያቄ ዓለም አቀፍ የሕግ ድጋፍና መሠረት ያለው መሆኑን አመልክተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1952 ባሳለፈው የውሳኔ ሃሳብ ቁጥር 390/5 የባህር በር ጉዳይ የሕልውና ጉዳይና አዎንታዊ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ ማስቀመጡን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ተነስታ የባህር በር የመጠቀም መብቷን ለማስከበር እንደ አማራጭ ልትጠቀምበት እንደምትችል አመልክተዋል።
በተጨማሪም የውሳኔ ሃሳቡ የባህር በር ጉዳይ ለቀጣናው ሰላምና ደኅንነት ቁልፍ መሆኑን እንደሚገልጽም ነው ያነሱት።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1982 በጃማይካ የተፈረመው የዓለም የባህር ሕግ ስምምነትም የባህር በር የሌላቸው አገራት ወደብ ካለበት ቦታ የመድረስና የመመለስ እንዲሁም በባህር ውስጥ የሚገኙ ኃብቶችን ጭምር መጠቀም እንደሚፈቅድ አብራርተዋል።
ከዚህ አንጻር ሕጉ ኢትዮጵያ የባህር በሮችን የመጠቀም መብት እንዳላት ጠቅሰው፤ አጠቃቀሙ ከአገራት ጋር ባላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች አማካኝነት መፈጸም እንደሚቻል ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር መጠቀም የሚያስችሏትን ሕጋዊ ማዕቀፎች በሙሉ አሟጣ መጠቀም እንዳለበት የገለጹት ምሁሩ፤ ከአገራት ጋር የሚደረጉ ድርድርና ውይይቶች ቁልፍ ሚና አላቸው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ ከባህር በርና አማራጭ ወደቦች ጋር በተያያዘ ያነሱት ሃሳብም የሰጥቶ መቀበል መርህ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ያነሳችው ሃሳብ የጋራ ተጠቃሚነትን ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ለቀጣናው አገራትና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስረዳት እንደሚጠበቅም ነው የሕግ ምሁሩ የተናገሩት።
የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪው ዶክተር ሄኖክ ጌታቸው በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ የባህር በርና የአማራጭ ወደቦች ተጠቃሚነት ጉዳይ ለብዙ ጊዜ ሲነሳ የነበረ ጥያቄ መሆኑን አስታውሰዋል።
የተጠቃሚነቱ ጉዳይ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ከምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ጋር የሚጣጣም ትክክለኛ ጥያቄ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
ለኢትዮጵያ በቀጣናው ያሉ ጥቅሞችን በውል ለመረዳትና ለመከታተል እንዲሁም ከሌሎች አገራት ጋር ትብብር በመፍጠር ፍላጎቷን ለማሳካት ያስችላታልም ብለዋል።
በቀጣናው አካባቢና ዙሪያ ባሉ ጉዳዮች ኢትዮጵያ በመገለል መቆየት ስለማትችል በሚነሱ የተለያዩ ሃሳቦች ምክክር ለማድረግ እንደሚያስችላትም ነው ተመራማሪው የተናገሩት።
የባህር በር ተጠቃሚነት ጉዳይ በቀጣናው የጋራ ልማትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የሌሎች አገራትን ብሔራዊ ጥቅም የማይጋፋና የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገና ዓለም አቀፍ ሕጎችን መሠረት ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም ጉዳዩን ለቀጣናው አገራትና ለዓለም አቀፍ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ በአግባቡ በማስረዳት ተጠቃሚነቷን እውን ማድረግ አለባት ብለዋል።