ቀጥታ፡

ተቋማት የምርትና አገልግሎት የጥራት ደረጃዎችን በአግባቡ በመተግበር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል - የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2016 (ኢዜአ)፦ ተቋማት የምርትና የአገልግሎት የጥራት ደረጃዎችን በአግባቡ በመተግበር ለአገሪቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጥሪ አቀረበ።  

ኢንስቲትዩቱ የዓለም አቀፍ የደረጃ ቀንን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ከአገር ውስጥ አምራቾች፣ አስመጪዎች፣ ላኪዎች፣ አከፋፋዮችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል። 

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሠረት በቀለ በዚሁ ጊዜ፤ የምርቶች ጥራት ቁጥጥር ሥራ ለአገር ዘላቂ ልማት መሳካት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል። 

በሁሉም ዘርፎች የወጡ ደረጃን በአግባቡ በመተግበር የአገሪቱ የምርትና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸው፤ ለዚህም ሁሉም በኃላፊነት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሰሃረላ አብዱላሂ በበኩላቸው፤ በአገሪቱ የወጡ ደረጃዎችና ደረጃዎቹን ገቢራዊ ለማድረግ የሚሰሩ ቁጥጥሮች ለአገሪቱ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል። 


 

የትኛውም ዓይነት ምርቶች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡና ከአገር ውስጥ ሲወጡ ጥራታቸውን እንዲጠብቁ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሚሰሩ ሥራዎች ሊጠናከሩ ይገባል ነው ያሉት።

የቃሊቲ የምግብ አክሲዮን ማኅበር ሥራ አስኪያጅ እዩኤል ለገሰ እና የኢትዮጵያ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የነዳጅ ጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት ኃላፊ ስዩም አራጋው፤ የየዘርፋቸውን የጥራት ደረጃ ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃም የዘርፉ የጥራት ደረጃዎች ወጥተው መተግበር መቻላቸው  ለተጠቃሚው ሕዝብና ለአገር ዘላቂ የኢኮኖሚ ግንባታ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።  

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም