በተያዘው የመኸር ወቅት በሰብል ከተሸፈነ የእርሻ መሬት 41 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል - የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በተያዘው የመኸር ወቅት በሰብል ከተሸፈነ የእርሻ መሬት 41 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል - የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2016 (ኢዜአ)፦ በተያዘው የመኸር ወቅት በሰብል ከተሸፈነ 532 ሺህ ሄክታር መሬት 41 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዑስማን ሱሩር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የመኸር ሰብል ምርታማነትን ለማሻሻል በከፍተኛ ንቅናቄ ሲመራ ቆይቷል።
በንቅናቄውም የክልሉን የግብርና ፀጋዎች በማልማት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የገቢ ምርትን መተካት፣ የወጪ ምርትን ማሳደግና ለኢንዱስትሪው ግብዓት የሚውሉ ምርቶችን ለማምረት ግብ ተይዞ ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰሩ የማሳ ዝግጅትና የሜካናይዜሽን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ውጤታማ በመሆናቸው በክልሉ ከሚመረቱ ቋሚ ሰብሎች በተጨማሪ በቆላ፣ ደጋና ወይና ደጋ አካባቢዎች አትክልት፣ ፍራፍሬና እንሰት በስፋት ማልማት እንደተቻለ ተናግረዋል።
በዚህም በሰብል ከተሸፈነ 532 ሺህ ሄክታር መሬት ከ 41 ነጥብ 7 ሚሊዬን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።
የመኸር ሰብል ለመሰብሰብ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በመኸር ሰብል የተደረገው ንቅናቄም የተቀመጠውን ግብ ማሳካት እንደሚያስችሉ ጠቅሰዋል።
የድኅረ-ምርት ብክነት፣ የግሪሳ ወፍ፣ የቢጫ ዋግና ሌሎች የሰብል በሽታዎች በሰብል ምርታማነት ላይ ተጽዕኖ እንዳያስከትሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ግብርና ተከታታይነት ያለው ሥራ እንደሚጠይቅ በመጥቀስ፤ የክልሉን የመሬት፣ የውኃና የሰው ኃይል ፀጋ አቀናጅቶና አስተባብሮ በመምራት ለዘርፉ ስኬታማነት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በመስኖ ልማት የተጀመሩትን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎችን ለማስቀጠል ከመኸር ወቅት ሰብል አሰባሰብ ሂደት ጎን ለጎን ለማስኬድ ንቅናቄ እንደሚካሄድ ገልፀዋል።
በክልል አቀፍ ንቅናቄ የመኸር ሰብል አሰባሰብ፣ የበጋ መስኖና የአረንጓዴ አሻራ ቅድመ-ዝግጅት ሥራና በሌማት ትሩፋት የተመጋገበ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በ132 ሺህ ሄክታር መሬት የበጋ መስኖ ለመሸፈን የቅድመ-ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተው፤ ከዚህም 35 ሚሊዬን ኩንታል ምርት ለማግኘት ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል።
በበጋ መስኖ ስንዴም በክልሉ ያሉ ፀጋዎችን በሚገባ በማልማት በ11 ሺህ ሄክታር መሬት 435 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት ግብ መቀመጡን ገልፀዋል።
በክልሉ የከምባታ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ራማቱ ለላጎ በበኩላቸው፤ የአርሶ አደሩን የሰብል ምርታማነት ለማሳደግ በኩታገጠም ስንዴ አስተራረስ ዘዴ እየተተገበረ መሆኑን ገልፀዋል።
የሰብል ምርታማነትን ማሻሻል የሚያስችል የግብዓት አቅርቦትና ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም እንዲሁ።
አስተያየታቸውን የሰጡ አርሶ አደሮችም የኩታገጠም አስተራረስ ዘዴ በምርት እድገት ላይ ከፍተኛ ጠቀሜታ እያስገኘላቸው መሆኑን ገልፀዋል።
አርሶ አደር ደስታ ቡልጬ፤ በኩታገጠም ሰብል ልማት የአስተራረስ ዘዴን በመከተል ካለሙት ስንዴ የተሻለ የሰብል ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
ሌላኛው አርሶ አደር አሹሮ ዮሐንስ የኩታገጠም አስተራረስ ዘዴን በመከተላቸው ምርታማነታቸው ማደጉን ጠቁመዋል።