ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ህገወጥ የጦር መሣሪያን ለመቆጣጠር የሚያስችል የመረጃ ቋት ተግባራዊ ሊያደርግ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ህገወጥ የጦር መሣሪያን ለመቆጣጠር የሚያስችል የመረጃ ቋት (Software) ተግባራዊ እንደሚደረግ ገለፀ።

በሀገር ደረጃ የጦር መሳሪያ በአንድ የመረጃ ቋት በመያዝ ህገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖለስ ስትራቴጂክ አመራሮች ባካሄዱት ውይይት ላይ ተገልጿል።

የጦር መሣሪያ አስተዳደርና የጥበቃ ተቋማት ቁጥጥር መምርያ ኃላፊ ኮሚሽነር ዘካሪያስ ይርጋለም፣ የጦር መሣሪያ ሲስተሙ በአጠቃላይ የሙከራ ስራ እየሰራ እንዳለ ጠቅሰው ለስራው መሳካት አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች እንዲሟሉና መረጃዎች ወደ በለጸገው ሶፍትዌር እንዲገቡ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የጦር መሣሪያ ሲስተሙ ወደ ሙሉ ትግበራ ሲገባ ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ላይ ቁጥጥርና ክትትል ለማድረግ ከፍተኛ እገዛ እንደሚፈጥር ኮሚሽነር ዘካሪያስ ይርጋለም መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል።

የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ 1177/2012 መሠረት ህገወጥ የጦር መሣሪያን ለመቆጣጠር የሚያስችል የመረጃ ቋት በሀገሪቱ ተግባራዊ እንዲሆን RECSA (Regional Centre on Small Arms and Light Weapons) ከተባለ ድርጅት ጋር ውይይት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም