ቀጥታ፡

የመከላከያ ሠራዊቱ በሁሉም ወታደራዊ መስኮች የሚሰጠውን ግዳጅ በብቃት የሚፈጽም ሕዝባዊ ሠራዊት ነው- የሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሁሉም ወታደራዊ መስኮች የሚሰጠውን ግዳጅ በብቃት የሚፈጽም ሕዝባዊ ሠራዊት ነው ሲሉ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያውያን ለሠራዊቱ የሚያከናውኑት የደጀንነት ተግባር እጅግ የሚያኮራ መሆኑንም የሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች ተናግረዋል፡፡

ኢዜአ በመጪው ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም የሚከበረውን የመከላከያ ሠራዊት ቀን ምክንያት በማድረግ የመከላከያ ሠራዊት ውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ እና በመከላከያ ሚኒስቴር የሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

እለቱ ኢትዮጵያ በዘመናዊ መልኩ የራሷን ሠራዊት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ ያቋቋመችበትን ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ.ም መነሻ በማድረግ የሚከበር ነው፡፡

የሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የሠራዊቱን ተልዕኮውን የመፈጸም አቅም ያሻሻሉ የለውጥ ሥራዎች መከናወናቸውንም ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡

ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ፤ ሠራዊቱ በአሁኑ ወቅት በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ፣ በአደረጃጀት፣ በሎጂስቲክስ፣ በሥነ-ልቦና፣ በትምህርትና ሥልጠና እጅግ በተደራጀ መንገድ መገንባቱን ተናግረዋል።

የመከላከያ ሠራዊት የግንባታ መሠረቱ ሕዝብ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ሠራዊቱ ሕዝባዊ ባህሪን የተላበሰና የድሎቹ መሠረት ደጀኑ ሕዝብ መሆኑን በጽኑ እንደሚያምን ገልፀዋል፡፡

ሠራዊቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተሰጠውን ግዳጅ በብቃት መፈጸም በሚያስችለው ቁመና ላይ እንደሚገኝም ጨምረው ተናግረዋል፡፡


 

በመከላከያ ሚኒስቴር የሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ በበኩላቸው፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ሠራዊቱ ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ በሆነና ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ባሳተፈ አግባብ መገንባቱን ተናግረዋል፡፡

ሠራዊቱ ከራስ በላይ ለአገርና ሕዝብ በሚል መርህ እንደሚመራ ገልጸው፤ ይህም የኢትዮጵያን ህልውና ለመጠበቅ ከሚሰጠው ግዳጅ ባለፈ በሰላም ማስከበር ተልዕኮም ውጤታማ ሥራ እንዲያከናውን አስችሎታል ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ሠራዊቱ በተሰማራበት ሰላም የማስከበር ተልዕኮ ፍቅርና ክብር የሚቸረው ሆኗል ነው ያሉት።

ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት የሚያስጠብቅና ጠንካራ መሆኑ እንቅልፍ የነሳቸው አንዳንድ አካላት በሐሰተኛ መረጃ ስሙን ለማጥፋት እንደሚሞክሩም የሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች ተናግረዋል፡፡

ሠራዊቱ በአንድ እጁ የሀገርና የሕዝብ ደኅንነት እያስከበረ በአንድ እጁ ደግሞ ከአርሶ አደሩ ጋር ተሰልፎ፣ እርሻ የሚያረስ፣ ሰብል የሚሰበስብና በልማት ሥራ የሚሳተፍ ነው ብለዋል።

ሕዝቡ የአገር ህልውና ጠላቶችን ሴራ በመገንዘብ ለሠራዊቱ የሚያደርገውን የደጀንነት ሥራ አጠናክሮ መቀጠሉንም አውስተዋል፡፡

አሁን ላይ ሠራዊቱ ዘመኑን በሚዋጅ አግባብ በሁሉም ወታደራዊ መስኮች በተሟላ አደረጃጀትና የግዳጅ መፈጸም ብቃት ላይ እንደሚገኝም የሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች ጨምረው ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም