ለብልጽግና ፓርቲ አመራሮች እየተሰጠ ያለው ስልጠና ችግሮችን በመፍታት የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አቅምን ይፈጥራል-ሰልጣኞች - ኢዜአ አማርኛ
ለብልጽግና ፓርቲ አመራሮች እየተሰጠ ያለው ስልጠና ችግሮችን በመፍታት የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አቅምን ይፈጥራል-ሰልጣኞች
ባህር ዳር፣ጥቅምት 6/2016 (ኢዜአ)፦ ለብልጽግና ፓርቲ አመራሮች እየተሰጠ ያለው ስልጠና ችግሮችን በመፍታት የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አቅምን እንደሚፈጥር ተገለጸ።
“ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ሃሳብ ስልጠናውን እየተከታተሉ የሚገኙ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ስልጠናው የአመራሩን አቅመ በማጎልበት ልማትን ለማፋጠን የሞራል ስንቅ የሚፈጥር ነው።
ከሰልጣኞች መካከል አቶ በቀለ ደቻሳ እንደገለጹት፤ ስልጠናው እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ የፓርቲው አመራር አባላት በጋራ የሚወስዱት መሆኑም ከዚህ ቀደም ከተሰጡት ስልጠናዎች የተለየ ያደርገዋል።
ስልጠናው የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በአግባቡ የሚያስገነዝብ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለአመራር አባላቱ በጋራ በመግባባት አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ መነሳሳትንና ቁርጠኝነትን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
“ስልጠናው ህብረ-ብሔራዊነትንና የጋራ አንድነትን የሚያጠናክር ነው”ያሉት ደግሞ ሌላው የስልጠናው ተሳታፊ አቶ አለሙ ስንኩርት ናቸው።
ስልጠናው የኢትዮጵያ ታሪክና ትርክትን በአግባቡ የሚያስገነዝብ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ ህብረ - ብሔራዊ አንድነትን መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያን ማበልጸግ እንደሚቻል ተናግረዋል።
ሌላኛዋ ተሳታፊ ወይዘሮ ህይወት ገብረእየሱስ በበኩላቸው፤ ስልጠናው በአገሪቷ ያለው አመራር እርስ በእርሱ እንዲተዋወቅ ዕድል የፈጠረ እንደሆነም ተናግረዋል።
በተጨማሪም የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ በማስቻል የአመራርነት አቅምን የሚያጎለብት እንደሆነም ገልጸዋል።