በአማራ ክልል ሰሜን ወሎና ዋግኽምራ ብሄረሰብ ዞኖች ለሚገኙ የጤና ተቋማት 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎና ዋግኽምራ ብሄረሰብ ዞኖች ለሚገኙ የጤና ተቋማት 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ
ደሴ፤ ጥቅምት 6/2016 (ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል ሰሜን ወሎና ዋግኽምራ ብሄረሰብ ዞኖች ለሚገኙ የጤና ተቋማት 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስና መድሃኒት ድጋፍ ተደረገ።
ድጋፉን ያደረገው 'ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ' ሲሆን የድርጅቱ የሰሜን ምስራቅ አማራ አደጋ መከላከልና ምላሽ ሰጭ ተወካይ ዶክተር አበባው ሲሳይ እንደገለጹት፤ የጤና ተቋማትን መልሶ በማቋቋም ለህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል እገዛ እየተደረገ ነው፡፡
በዚህም በሰሜን ወሎና ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች የጤና ተቋማት 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስና መድሃኒት ዛሬ ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
ከድጋፉ መካከል የደም ግፊት መለኪያ መሳሪያ፣ የጽንስ ማዳመጫ፣ የተለያዩ ማሽኖችን ጨምሮ ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶችና ልዩ ልዩ መድሃኒቶች ይገኙበታል ብለዋል፡፡
በምስራቅ አማራ የሚገኙ ጤና ተቋማት ለህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት መስጠት እስከሚችሉ ድረስ የተጀመረው ሁለተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ተወካይ አቶ ሞገስ ቸርነት በበኩላቸው፤ የጤና ተቋማት ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ መልሶ የማቋቋም ስራ እየተከናወነ ነው፡፡
የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ሲሆን አሁንም በመልሶ ማቋቋሙ ስራው የባለድርሻ አካላት ድጋፍ መጠናከር አለበት ብለዋል።
'ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ' ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ ድጋፉ በጤና ተቋማት የገጠመውን የህክምና ቁሳቁስና የመድሃኒት እጥረት ለማቃለል እንደሚያግዝም ገልጸዋል፡፡
''የተደረገው መሰረታዊ መድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እጥረቱን ከማቃለል ባለፈ ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንድንሰጥ ያግዛል'' ያሉት ደግሞ የሀብሩ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ አስችል ስማቸው ናቸው፡፡
'ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ' በምስራቅ አማራ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም በሎጅስቲክ፣ በፋይናንስ፣ በግብዓትና በሰው ኃይል የተለያየ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ተጠቅሷል።