ሀገራዊ ምክክሩ በተሳካ መልኩ እንዲከናወን የሚጠበቅብንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል - የአሶሳ ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ በተሳካ መልኩ እንዲከናወን የሚጠበቅብንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል - የአሶሳ ዞን ነዋሪዎች
አሶሳ፤ ጥቅምት 06/2016 (ኢዜአ) ሃገራዊ ምክክሩ የተሳካ እንዲሆን የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአሶሳ ዞን ተወካዮች ገለጹ ፡፡
የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ከማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ተወያይቷል፡፡
በወይይቱ ከተሳተፉት መካከል አቶ አቶም መሃመድ፣ በውይይትና በመግባባት ሀገርን ሠላም ማድረግ ይቻላል ብለዋል።
''በማያግባቡን ጉዳዮች ላይ በግልጽ በመነጋገር ለልጆቻችን የተረጋጋች ሃገርን ማስተላለፍ ያስችለናል'' ነው ያሉት፡፡
''ኮሚሽኑ በንግግርና በውይይት ዘላቂ ሠላም ለማምጣት የጀመረውን ጥረት ለማሳካት ሃላፊነቴን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ'' ብለዋል፡፡
በክልሉ ተደራጅተው ወርቅ በማምረት ላይ ከሚገኙ ሴቶች መካከል የሆነችው ወጣት ሐናን አድላን በበኩሏ በተሰማራችበት ዘርፍ ተጠቃሚ መሆን የቻለችው አካባቢዋ ሠላም በመሆኑ እንደሆነ ገልጻለች፡፡
ኮሚሽኑ በዜጎች መካከል መግባባት በመፍጠር ከድህነት ለመውጣት በሚደረገውን ጥረት አስተዋጽኦው የጎላ ነው የምትለው ወጣቷ፣ የኮሚሽኑን ዓላማና ተልዕኮ በኅብረተሰቡ ውስጥ በማስረጽ የድርሻዋን እንደምትወጣ ተናግራለች፡፡
አቶ ሚዛን ኡስማን በበኩላቸው ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው በመነጋገር ብቻ መሆኑን አመልክተው፣ ''ችግሮችን በውይይትና በምክክር መፍታትና አንድነታችንን ማጠናከር አለብን'' ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን ኮሚሽኑ ቤኒሻንጉል ጉሙዝን ጨምሮ በክልሎች ያካሄዳቸው መድረኮች ሕዝቡ በሃገራዊ ምክክሩ አስፈላጊነት እንደሚያምን አሳይቷል ብለዋል፡፡
ኅብረተሰቡ የቋንቋ፣ የባህልና ሌሎችም ልዩነቶች ሳያግዱት ለሀገራዊ ምክክሩ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን በማቅረብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ ዋናው ሃገራዊ ምክክር በአጭር ጊዜ እንዲጀመር ሁሉንም ዜጎች ያካተቱ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ ለዚህም የመወያያ አጃንዳዎችን እያሰባሰበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ምሁራንና የሃገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ለማሳተፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ኮሚሽነር ብሌን ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የሚያሰባስቡ የተሳታፊዎች ልየታ የሚያካሂድባቸው መድረኮች በክልሎች እያካሄደ ነው።