በአማራ ክልል እየተሻሻለ የመጣውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የህዝቡ ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት- ኮማንድ ፖስቱ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል እየተሻሻለ የመጣውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የህዝቡ ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት- ኮማንድ ፖስቱ
ባህር ዳር፤ጥቅምት 6/2016 (ኢዜአ)፡ - በአማራ ክልል በተከናወነው የተቀናጀ ስራ እየተሻሻለ የመጣውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የህዝቡ ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊና የኮማንድ ፖስቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ገለጹ።
በክልሉ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ መግለጫ ዛሬ ተሰጥቷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪና የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ እንዲሁም የኮማንድ ፖስቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በመግለጫቸው እንዳሉት፤ በክልሉ ተከስቶ የነበረው ችግር ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት አስከትሏል።
የክልሉ ህዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በመንጠቅ ችግር የፈጠሩ አካላት በሃይል ለመፍታት በሚፈጽሙት ድርጊት በህብረተሰቡ የእለት ከእለት እንቅስቃሴ ላይ ጫና መፍጠሩን ገልፀዋል።
በዚህም በሰዎችና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አውስተዋል።
በድርጊቱ ህዝቡን ለተባባሰ የኑሮ ውድነት፣ የስራ አጥነትና ሌሎች ችግሮች እንዲጋለጥ በማድረግ ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል።
በመከላከያ ሰራዊትና በክልሉ የጸጥታ ሃይሎች እየተከናወነ ባለ የሰላም ማስከበር ስራ አሁን ላይ የክልሉ ሰላም በዋና ዋና ከተሞችና ዞኖች እየሻሻለ መምጣቱን አስረድተዋል።
በቀጣይም እየተሻሻለ የመጣውን ሰላም በመጠቀም ህዝቡ የሚፈልገውን ዘላቂ የሰላም አየር ለማስፈን ሌት ከቀን እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በተቀናጀ መንገድ እየተከናወነ ያለውን የሰላምና መረጋጋት ስራ የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ መላው ህዝብ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በተለይም የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ተሰሚነት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው ብለዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞችም በየስራ ቦታቸው በመገኘት ለህዝባቸው ፈጣን፣ ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።