የጤና ባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ የሰመመን (አንስቴዥያ) የሕክምና አገልግሎት ለማስፋት እየተሰራ ነው - የጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የጤና ባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ የሰመመን (አንስቴዥያ) የሕክምና አገልግሎት ለማስፋት እየተሰራ ነው - የጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 6/2016(ኢዜአ)፡- የጤና ባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ የሰመመን (አንስቴዥያ) የሕክምና አገልግሎት ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
የሰመመን ሕክምና (አንስቴዥያ) የሰው ልጅ በቀዶ ሕክምና ምንም ዓይነት የሕመም ስሜት ሳይሰማው የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል የጤና አገልግሎት ነው።
የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አንስቴዮሎጂ ሐኪሞች ማኅበርና የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማኅበር ዓለም አቀፉን የሰመመን ሕክምና (አንስቴዥያ) ቀንን አክብረዋል።
በዓሉ "የማኅበረሰብ ግንዛቤ ለአንስቴዥያ ሕክምና ደኅንነት" በሚል መሪ ኃሳብ ተከብሯል።
በጤና ሚኒስቴር የቀዶ ጥገናና የአንስቴዥያ መርኃ-ግብር አስተባባሪ አብይ ዳዊት በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በጤናው ዘርፍ ትልቅ መሠረት ከጣሉ ግኝቶች ውስጥ አንዱ የሰመመን ሕክምና ነው።
ይህም በሕክምናው ላይ በርካታ ለውጦች እንዲመጡ ያስቻለ ግኝት መሆኑን ገልፀዋል።
የጤና ሚኒስቴር የሰመመን ሕክምና አገልግሎት ለማሻሻል ስትራቴጂዎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ በርካታ ተጨባጭ ሥራዎችን መሥራቱን ጠቁመዋል።
ለአብነትም የሥልጠና ማኑዋሎችን በማዘጋጀት የዘርፉን ባለሙያዎች በማሰልጠን አቅማቸውን የማሻሻል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የአገልግሎት አሰጣጡ በጥራትና በተደራሽነት አመርቂ ውጤቶች እያስመዘገበ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አንስቴዮሎጂ ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር አናንያ አባተ፤ ሕብረተሰቡ ስለ ሰመመን ሕክምና (አንስቴዥያ) ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዓለም አቀፉ የሰመመን ሕክምና ቀን መከበሩ ማኅበረሰቡ ስለ ሕክምናው በቂ እውቀት እንዲኖረውና ይህም ደግሞ ለሕክምና አሰጣጡ መቀላጠፍ አስተዋጽዖ አለው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት ሲራጅ አህመድ፤ የሕክምና አገልግሎቱ በጤና ጣቢያዎች እንዲሰጥ እየተሰራ ያለው ሥራ አበረታች መሆኑን ገልፀዋል።