10ኛው የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ጥቅምት 25 ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
10ኛው የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ጥቅምት 25 ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት6/2016 (ኢዜአ)፦10ኛው የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ጥቅምት 25ቀን 2016 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ለውድድሩ ተሳታፊዎች ከ300 ሺህ ብር በላይ ሽልማት መዘጋጀቱም ታውቋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዮሐንስ እንግዳ፤ ለኢዜአ እንደገለጹት የጎዳና ላይ ሩጫው ፌዴሬሽኑ በቋሚነት ከሚያካሂዳቸው ዓመታዊ ውድድሮች አንዱ ነው።
በውድድሩ ላይ በሁለቱም ጾታዎች ከክለቦች፣ ከክልሎችና በግል የሚወዳደሩ ከ500 በላይ አትሌቶች ይሳተፋሉ ብለዋል።
ውድድሩ በአዋቂዎችና ወጣቶች እንዲሁም በወንዶች ከ50 ዓመት በላይና በታች እንዲሁም በሴቶች ከ50 ዓመት በታች እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።
የጎዳና ላይ ሩጫው ለአትሌቶች የውድድር ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ተተኪዎችን ለማፍራት አስተዋጽኦ ያደርጋልም ነው ያሉት።
አትሌቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚከናወኑ የጎዳና ላይ ውድድሮች አቋማቸውን ለመፈተሽ እንደሚያግዛቸውም ጠቅሰዋል።
በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ለሚያሸንፉ አትሌቶች እያንዳቸው የ40 ሺህ ብር ሽልማት ይበረከትላቸዋል ብለዋል።
ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ለሚወጡ አትሌቶች በአጠቃላይ ከ300 ሺህ ብር በላይ ሽልማት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ጥቅምት 27ቀን 2015 በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደው ዘጠነኛው የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በወንዶች አትሌት ፋንታሁን ሁነኛው፤ በሴቶች አትሌት አፀደ ባይሳ ማሸነፋቸው የሚታወስ ነው።
በወንዶች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሴቶች ኦሮሚያ ፖሊስ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ መሆናቸው አይዘነጋም።