ቀጥታ፡

በሰው ሰራሽ የእንስሳት ዝሪያ ማሻሻያ ዘዴ ከተዳቀሉ ከብቶቻችን የተሻለ ጥቅም እያገኘን ነው - የኢሉባቦር ዞን አርሶ አደሮች

መቱ ፤ጥቅምት 06/2016 (ኢዜአ):-በሰው ሰራሽ የእንስሳት ዝሪያ ማሻሻያ ዘዴ ከተዳቀሉ ከብቶቻቸው ጥሩ ውጤት እያገኙ መሆኑን በኢሉባቦር ዞን አርሶ አደሮች ገለፁ።

እንስሳትና እንስሳት ዝርያ ማሻሻልና የስጋና የወተት ተዋጽኦ መጠንና ጥራት ማሳደግ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ውስጥ ከተያዙት ዋና ዋና ተግባራት አንዱ ነው።

ጥራት ያለው የወተትና የስጋ ምርት ለማግኘት ደግሞ እንስሳቱን በሰው ሰራሽ ስነ ዘዴ የማዳቀል ስራ አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም።  

በኢሉባቦር ዞን ባሉ ወረዳዎችም አርሶ አደሮቹ በሰው ሰራሽ ዘዴ እንስሳቱን በማዳቀል ከውጤቱም ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ይገልጻሉ።

በዞኑ የዲዱ ወረዳ ነዋሪ አቶ አበራ ጆቴ ከዚህ ቀደም በተለመደው መንገድ ያረቡ ከነበሩ ከብቶቻቸው የሚያገኙት የወተት ምርት ከድካማቸው ጋር ሲነፃፀር እምብዛም አለመሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የሚወለዱ ጥጆችና ወይፈኖች ለገበያም ሆነ ለወተት ምርት እንዲሁም ለእርሻ የሚደርሱት በትንሹ ከስድስት ዓመት በኋላ መሆኑን አቶ አበራ አከለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰው ሰራሽ የእንስሳት ዝሪያ ማሻሻያ ዘዴ ከተዳቀሉ ከብቶቻቸው እያገኙ ያሉት የወተት ምርት ከእጥፍ በላይ መጨመሩንና ተጠቃሚነታቸው ማደጉን ተናግረዋል።

ቀድሞ በቀን ከሁለት ሊትር በላይ ወተት አግኝተው እንደማያውቁ ያስታወሱት አቶ አበራ፤ በዚህ ቴክኖሎጂ ከተዳቀሉ ላሞች ግን በቀን በአማካይ እስከ ስድስት ሊትር ወተት ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ከዚህ በፊት የነበራቸው ላሞች የሚወልዷቸው ጥጆች አድገው በገበያ ጥሩ ገንዘብ ለማስገኘትም ሆነ የወተት ምርት የሚሰጡበት ጊዜ ከተዳቀሉትጋር ሲነፃፀር ረዥም ጊዜ የሚያስጠብቅ መሆኑን አንስተዋል።

በሰው ሰራሽ ዘዴ ተዳቅለዉ የሚወለዱ ጊደሮችም ከሶስት ዓመት በታች በሆነ ጊዜ ደርሰው የሚወልዱ መሆናቸውን በማንሳት።

ወይዘሮ ሊኪቱ አብዲሳ በበኩላቸው በሰው ሰራሽ ዘዴ ከተዳቀሉ ላሞቻቸው እያገኙ ያሉት የወተት ምርት መጠን የጨመረ መሆኑን አንስተው፤ ይህም የተሻለ ጥቅም እንዲያገኙ ያስቻላቸው መሆኑን ይገልፃሉ።

በመሆኑም ያሏቸውን ላሞች ሁሉ በዚህ ቴክኖሎጂ ታግዘዉ ዝሪያቸውን በማሻሻል ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን መወሰናቸውን ተናግረዋል።

አቶ አህመድ ከማል ደግሞ በዚህ ሰው ሰራሽ ዘዴ ዝሪያቸው ከተሻሻለ ከብቶች የሚገኙ ወይፈኖች በአጭር ጊዜ ለስጋ ምርት የሚደርሱ በመሆናቸው በገበያ የሚያወጡት ዋጋ ከፍተኛ ነው ይላሉ።

በወተት ምርትም ከፍተኛ ብልጫ ያላቸው መሆኑን አንስተው እርሳቸውም በተያዘው ዓመት ያላቸውን ላሞች በሙሉ በሰው ሰራሽ የእንስሳት ዝሪያ ማሻሻያ ዘዴ ለማዳቀል መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።    

በዲዱ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የእንስሳት ሀብት ልማት ባለሙያ ዶክተር ተመስገን ዋቅሹም በሰው ሰራሽ የእንስሳት ዝሪያ ማሻሻያ ዘዴ የሚዳቀሉ ከብቶች ውጤታማነት በባህላዊ ዘዴ ከሚደረገዉ የእንስሳት ልማት የተሻለ የወተትና የስጋ ምርት የሚያስገኙ ይሆናሉ ብለዋል።

በቴክኖሎጂው ከሚዳቀሉ ከብቶች የሚፈለገውን ውጤት ለማግኘት በመኖ፣ በመጠለያና በጤናቸው አስፈላጊው እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባም በማከል።

በዞኑ በተያዘው ዓመት ከ45 ሺህ በላይ የሚሆኑ ላሞችን በሰው ሰራሽ ዘዴ ለማዳቀል ታቅዶ ወደ ስራ የተገባ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የኢሉባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አወል መሐመድ ናቸው።

የእንስሳትና እንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን ምጠንና ጥራት በመጨመር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የእንስሳት ዝሪያን በሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ  የማሻሻል ስራ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም