የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መርህ ለቀጣናዊ ትስስር፣ የጋራ እድገትና ተጠቃሚነት ፋይዳው የላቀ ነው- የመስኩ ተመራማሪ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መርህ ለቀጣናዊ ትስስር፣ የጋራ እድገትና ተጠቃሚነት ፋይዳው የላቀ ነው- የመስኩ ተመራማሪ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 06/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መርህ ለቀጣናዊ ትስስር፣ የጋራ እድገትና ተጠቃሚነት የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የስትራቴጂ ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የመስኩ ተመራማሪ ጃፋር በድሩ ገለጹ።
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መርህ የባለ ብዙ ወገን የትብብር ግንኙነትን በመከተል ለቀጣናዊ ትስስር፣ የጋራ እድገትና ተጠቃሚነትን የሚያበረታታ መሆኑ ይታወቃል።
የውጭ ዲፕሎማሲዋ የተቃኘው ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ መስጠት፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ማጠናከርና ሁለንተናዊ ትብብርንም መፍጠር ነው።
ከዚህ አኳያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የስትራቴጂ ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የመስኩ ተመራማሪ ጃፋር በድሩ፤ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መርህ ለቀጣናዊ ትስስር፣ የጋራ እድገትና ተጠቃሚነት የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የባለ ብዙ ወገን የትብብር ግንኙነት የጋራ ልማትና ምጣኔ ኃብታዊ እድገትን ከማሳለጥ ባለፈ ዘርፈ-ብዙ ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
ቀጣናዊ ትስስሩን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ አቅሞች መኖራቸውን ገልጸው፤ እነዚህን አስቻይ ሁኔታዎች አሟጦ መጠቀም ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የትብብር ዲፕሎማሲን በማጠናከር የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጎልበት የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ አገራት ይበልጥ ተቀራርበው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤን በማጉላትና አህጉራዊ ትብብርን በማጠናከር ረገድ እያደረገችው ያለው ጥረት የሚበረታታና በሁሉም ሊደገፍ የሚገባው ነው ብለዋል።
የአፍሪካን ሁለንተናዊ ልማትና ትብብር በማጠናከር ለጋራ እድገትና ብልጽግና መስራት ይገባልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በ2016 ዓ.ም. በዲፕሎማሲው መስክ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት ለማጠናከር የምትሰራ መሆኑን ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፤ በፓርላማ ንግግራቸው ማረጋገጣቸው ይታወሳል።