የኢትዮጵያና ቻይና ግንኙነት በዲፕሎማሲና ኢኮኖሚ መስክ እንዲሁም በህዝብ ለህዝብ ትስስር ረገድ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ይገኛል- አምባሳደር ተፈራ ደርበው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ቻይና ግንኙነት በዲፕሎማሲና ኢኮኖሚ መስክ እንዲሁም በህዝብ ለህዝብ ትስስር ረገድ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ይገኛል- አምባሳደር ተፈራ ደርበው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 05/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያና ቻይና ግንኙነት በዲፕሎማሲ እና ኢኮኖሚው መስክ እንዲሁም በህዝብ ለህዝብ ትስስር ረገድ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ እንደሚገኝ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ቻይና ቤጂንግ መግባታቸው ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቻይና ከሚያደርጉት የስራ ጉብኝት ጎን ለጎን ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የምጣኔ ኃብት ትብብር በሚያጠናክሩባቸው መንገዶች ዙርያ ተወያይተዋል።
በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው እንደገለጹት የቻይናና የኢትዮጵያ ግንኙነት ባለፉት 30 አመታት በላቀ ሁኔታ አድጓል።
ቻይናና ኢትዮጵያ በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊና በባለ ብዙ መረኮች ላይ ተመሳሳይ አቋም በማራመድ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን በጋራ እንደሚሰሩ ነው ያመለከቱት።
ኢትዮጵያና ቻይና በዲፕሎማሲ እና ኢኮኖሚው መስክ በተለይም በኢንቨስትመንት፣ በንግድና ቱሪዝም ዘርፍ ያላቸው ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል ያሉት አምባሳደሩ በህዝብ ለህዝብ ትስስር ረገድም ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው አውስተዋል።
በርካታ ኢትዮጵያውያን በትምህርት እድልና በሌሎች መስኮች ወደ ቻይና መጥተው ተጠቃሚ መሆናቸው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር ማስቻሉን ነው ያብራሩት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቻይና እያደረጉ ያሉት የስራ ጉብኝትም የሁለቱን ሀገራት የረጅም ዘመናት ግንኙት ጥልቀት እንዲኖረውና ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርስ መሆኑን አስታውቀዋል።