ሴቶች በቡናው ዘርፍ በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እንዲሰሩ ከማገዝ ጀምሮ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ሴቶች በቡናው ዘርፍ በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እንዲሰሩ ከማገዝ ጀምሮ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 5/2016 (ኢዜአ)፦ ሴቶች በቡናው ዘርፍ በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እንዲሰሩ ከማገዝ ጀምሮ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናገሩ።
በቡና ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ ዓለም አቀፍ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በጉባዔው የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ33 አገራት የተወጣጡ በዘርፉ እሴት ሠንሰለት የተሰማሩ ሴቶች፣ ቡና ገዥዎችና በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።
በመድረኩ በዘርፉ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚረዱ የመፍትሔ ኃሳቦች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል፤ ለዚህም የሚረዳ የጥናት ውጤቶች ይቀርባሉ ተብሏል።
በተጨማሪም አገራት በቡናው ዘርፍ ሴቶች የሚገጥማቸውን ችግሮች እንዴት ይፈታሉ? በፖሊሲና በአሠራር አካተው እንዴት ችግሮችን እየፈቱ ነው? በሚሉ ጉዳዮች የልምድ ልውውጥ ይደረጋል ተብሏል።
ኢትዮጵያ በቡናው መስክ ያላትን እምቅ አቅም የማስተዋወቅ ስራ እንደሚከናወንም እንዲሁ፡፡
ጉባኤው ዛሬና ነገ የሚካሄድ ሲሆን ከመጪው ረቡዕ ጥቅምት 7 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የጉባዔው ተሳታፊዎች በቀጣይ ቀናት በተመረጡ ቡና አብቃይ ሥፍራዎች ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሏል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤መንግሥት በዘርፉ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የአሰራር ማሻሻያዎች ተግባራዊ በማድረግ ጭምር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም በመሬት አጠቃቀም አዋጅ ሴቶች መሬት ባለቤትነት መብት የሚያረጋግጥ ስርዓት መዘርጋቱ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንዲያም ሆኖ ሴቶች በተለይም በቡናው ልማት ዘርፉ በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቅንጅታዊ አሰራሮች ሊጠናከሩ እንደሚገባም ነው አጽንኦት የሰጡት።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው በቡናው ዘርፍ ሴቶች የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በቡና ልማቱ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ ለዚህም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።
እንደ ዶክተር አዱኛ ገለጻ በቡና ልማት እሴት ሰንሰለቱ ውስጥ የሚሳተፉ ሴቶች አቅማቸው እንዲገነባ፣ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑና ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል ስትራቴጂ ተነድፎ ተግባራዊ ተደርጓል።
"ውሜን ኢን ኮፊ ኢትዮጵያ" የቦርድ ሊቀ መንበር ወይዘሮ ሳራ ይርጋ እንደተናገሩት፤ጉባኤው ኢትዮጵያ እንደ ቱሪዝም ሁሉ የቡና መዳረሻ መሆኗን ለውጭ ዜጎች ማሳየትን ማዕከል ያደረገ ነው።
በቡናው መስክ ያሉ ሴቶች በተለያዩ አገራት በዘርፉ ከተሰማሩ ሴቶች ጋር የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ሌላው የጉባኤው ዓላማ መሆኑን ነው ያብራሩት።
ከጉባኤው ጎን ለጎን ከ15 አገራት የመጡ ቡና አምራቾች ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት ኤክስፖ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።