ለሰንደቅ አላማ ክብርና ሀገራዊ አንድነት የዜጎችን ትብብር የሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ በልዩ ትኩረት እንሰራለን- የኢዜአ ሰራተኞች - ኢዜአ አማርኛ
ለሰንደቅ አላማ ክብርና ሀገራዊ አንድነት የዜጎችን ትብብር የሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ በልዩ ትኩረት እንሰራለን- የኢዜአ ሰራተኞች
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 5/2016 (ኢዜአ) ፦ ለኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ክብርና ሀገራዊ አንድነት የዜጎችን ትብብር የሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ በልዩ ትኩረት እንሰራለን ሲሉ የኢዜአ ሰራተኞች ገለጹ።
የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን "የሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንና ሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው" በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል።
የኢትዮጰያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) አመራርና ሰራተኞችም እለቱን ለሰንደቅ አላማው ክብር በሚመጥን መልኩ በደማቅ ስነ ስርአት አክብረዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የኢዜአ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ ለሀገር ሉአላዊነትና ለሰንደቅ አላማው ክብር በርካታ ጀግኖች መስዋእትነት ከፍለው ማለፋቸውን ገልጸዋል።
በዚህም የሀገር ክብር ተጠብቆና የህዝቦች ነፃነት ተከብሮ መዝለቁን ጠቅሰው የአሁኑ ትውልድም ይህንኑ ጠብቆ የማስቀጠል አደራ አለበት ብለዋል።
የሰንደቅ አላማ ቀን ሲከበርም ለሰንደቅ አላማ ክብር መስዋእትነት የከፈሉ ጀግኖችን ክብርና እውቅና በመስጠት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።
የሰንደቅ አላማውን ታሪክ፣ ክብርና ትርጉም በቅጡ በመረዳት ለጋራ ልማትና ዘላቂ ሰላም መስራት የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባልም ብለዋል።
ለሀገራዊ አንድነት ሰላምና ልማት በጋራ በመስራት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጉላት አበይት ጉዳዮች ስለመሆናቸው አንስተው የሀገርን ገጽታ ለማጉላትና ብሄራዊ መግባባት በመፍጠር ረገድ ኢዜአ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋለ።
ኢዜአ ለሀገር ክብር፣ ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረትም አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ ከተሳተፉት የተቋሙ ሰራተኞች መካከል ጋዜጠኛ ቀበኔሳ ገቢሳ እና ብሌን በቀለ፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከጥንት እስከዛሬ በጀግኖች መስዋእትነት በክብር የዘለቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የሰንደቁን ታሪክና ክብር በሚመጥን መልኩ በየዓመቱ መከበሩ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው በሙያቸው ከምንም በላይ የሀገርን ክብርና አንድነት በማስቀደም እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያዊያንን እሴቶች የሚያጎሉ፣ የሀገርን ገጽታ የሚገነቡና ሰላምን የሚያጸኑ ይዘቶች ላይ በስፋት የሚሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ክብርና ሀገራዊ አንድነት የዜጎችን ትብብር የሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ በልዩ ትኩረት እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።
የኢዜአ የህዝብ ግንኙነትና የስትራቴጂያዊ አጋርነት ዳይሬክተር ዮሃንስ ወንድይራድ፤ የአንድነት፣ የጽናትና ጀግንነት ምልክት የሆነውን ሰንደቅ አላማ ተገቢውን ክብር መስጠትና በጋራ ማክበር አስፈላጊ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በዜጎች መካከል አንድነትን፣ አብሮነትንና ብሔራዊ አንድነትን የሚፈጥሩ ዘገባዎችን ኢዜአ እየሰራ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።