ቀጥታ፡

ለሰንደቅ ዓላማችን ተገቢውን ክብር መስጠት ይገባናል- የሐረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ

ሐረር ፤ ጥቅምት 5 /2016 (ኢዜአ)  ፡-በጀግኖች አባቶቻችን መስዋዕትነት ተጠብቆ ለቆየው ሰንደቅ ዓላማችን  ተገቢውን ክብር መስጠት ይገባናል ሲሉ የሐረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ -ጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም  ገለጹ።

"ሰንደቅ ዓላማችን ለኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንና ለሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው” በሚል መሪ ሀሳብ 16ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ በሐረሪ ክልል ተከብሯል።

በወቅቱ  አፈ- ጉባኤው ፤ የኢፌዴሪ  ሰንደቅ ዓላማ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችና የሃይማኖት እኩልነትን የሚያንጸባርቅ ዓርማ መሆኑን ተናግረዋል።

ለሰንደቅ ዓላማው ክብር በርካታ ጀግኖች አባቶቻችን የህይወት መስዋዕትነት  መክፈላቸውን ጠቅሰው፤ ይህንን በማስጠበቅ  ተገቢውን ክብር መስጠት ይገባናል ብለዋል።

በተለይ ዘንድሮ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ስናከብር ታላቁ የኢትዮጵያ  ህዳሴ ግድብ አራተኛ ዙርና የመጨረሻው  የውሃ ሙሌት በስኬት ያጠናቀቅንበት ወቅት  በመሆኑ  ልዩ ያደርገዋል ሲሉ ጠቅሰዋል።

ሰንደቅ ዓላማችን ኢትዮጵያዊያን  በአለም አቀፍ መድረክ በኩራት የሚያውለበልቡትና የነፃነት ተምሳሌት ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች  ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ ናቸው።

በዓሉ የሚከበረው ዜጎች ስለ ሰንደቅ ዓላማ ምንነት፣ ክብርና ትርጓሜ በተገቢው መንገድ ተገንዝበው ተገቢውን ክብር እንዲሰጡት ለማስቻል እንደሆነም ገልጸዋል።

በበዓሉ ላይ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱሰላምና የሐረሪ ጉባኤ  አፈ ጉባዔ አቶ ሙህተዲን አህመድ  የሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ ሥርዓት ያከናወኑ ሲሆን ፤ ታዳሚዎችም የሀገርን ነጻነት ለማስጠበቅ፣ ሰላምና ልማትን ለማጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ በቃለ መሃላ አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም