16ኛው የሰንደቅ አላማ ቀን በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
16ኛው የሰንደቅ አላማ ቀን በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ተከበረ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2016 (ኢዜአ)፡- 16ኛው የሰንደቅ አላማ ቀን በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች “የሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ ለሕብረብሄራዊ አንድነታችንና ሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል።
የሰንደቅ ዓለማ ቀን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ በጁቡቲ፣ በሕንድ፣ ኳታር፣ ጣሊያን፣ ብሪታንያ፣ ታንዛንያ እንዲሁም ጃፓን በሚገኙ ኤምባሲዎች ነው የተከበረው።
በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተከበረ ሲሆን በአከባበሩ ላይ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት አምባሳደር ዑመር ሁሴን ሰንደቅ ዓላማ የብሔራዊ አንድነት መገለጫ ነው ብለዋል።
አምባሳደሩ፤ “በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁላችሁ በተሰማራችሁበት በየትኛውም ዘርፍ የአገራችሁ ተወካይ ዲፕሎማት እንደመሆናችሁ በአርበኛነት ስሜት ሠንደቅ ዓላማችንን ከፍ በሚያደርግ ትጋት እና ስነ ምግባር የበኩላችሁን እንድትወጡ ጥሪ አቀርባለሁ" ብለዋል።
በተመሳሳይ በዓሉ በጁቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ የኤምባሲው ሰራተኞች፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሠራዊት አታሼዎች እና በጁቡቲ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ተወካዮች በተገኙበት ተከብሯል።
እለቱን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ይህን ቀን ስናስብ ዛሬም ኢትዮጵያውያን ለመጠበቅ የሃገሩን ባንዲራ ይዞ ህይወትን እየሰዋ ላለው ለመከላከያ ሠራዊታችን ክብር በመስጠት እና አገራችን በዲፕሎማሲ ዘርፍ ስኬታማ ለማድረግ ጠንክሮ በመስራትም ጭምር ነው ብለዋል።
ቀኑ በህንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሳደር ደመቀ አጥናፉን ጨምሮ የኤምባሲው ሰራተኞች እንዲሁም በህንድ የኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ አባላት በተገኙበት ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት በአምባሳደር ደመቀ አጥናፉ በዓሉን ስናከብር ህብረ ብሄራዊ አንድታችንን ለማጠናከር፣የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ እንዲሁም ልማትን ለማፈጠን ቁርጠኝነታችንን ማደስ ይገባናል ብለዋል።
በዓሉ በኳታር የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተከበረ ሲሆን አምባሳደር ፈይሰል አልይ ኢብራሂም ሰንደቅ ዓላማችን የብዙዎች የአካልና የህይወት መሰዋዕትነት የተከፈለባት ሉዓላዊት ሀገራችንን የምትወክል የአንድነታችንና የአብሮነታችን ዓርማ ነው ብለዋል።
አምባሳደሩ አክለው ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያውያን የነፃነት፣ የጽናት፣ ሀገርን የመውደድና የአልበገር ባይነት መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓሉ በጣልያን፣ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በታንዛንያ እንዲሁም ጀፓን በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ተከብሯል።

በተመሳሳይ 16ኛው የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል “የሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ ለሕብረብሔራዊ አንድነታችንና ሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው” በሚል መሪ ቃል በጅዳ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ቆንስላ ጽ/ቤት በድምቀት የተከበረ ሲሆን በበዓሉ አከባበር ላይ አምባሳደር ሙሉጌታ ከሊል በጅዳ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ቆንስል ጄኔራል፣ ዲፕሎማቶች፣ የቆንስላ ጄኔራሉና የኮሚኒቲ ማህበር ጽህፈት ቤት ሰራተኞች ተገኝተዋል።