ሰንደቅ ዓላማችን የነጻነታችን መገለጫና የኩራታችን ምንጭ ነው - የሰንደቅ ዓላማ ቀን አከባበር ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሰንደቅ ዓላማችን የነጻነታችን መገለጫና የኩራታችን ምንጭ ነው - የሰንደቅ ዓላማ ቀን አከባበር ተሳታፊዎች
አምቦ/ነገሌ ቦረና/ነቀምቴ/ግምቢ ፤ ጥቅምት 5/2016(ኢዜአ) ...ሰንደቅ ዓላማችን የነጻነታችንና የወንድማማችነታችን መገለጫ የኩራታችን ምንጭ ነው ሲሉ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የሰንደቅ ዓላማ ቀን አከባበር ተሳታፊዎች ገለጹ።
የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ''የሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ ለሕብረ - ብሔራዊ አንድነታችንና ሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው'' በሚል መሪ ሐሳብ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን፣ በምስራቅ ቦረና ዞን ነገሌ ቦረና ከተማ፣ በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ እና በምዕራብ ወለጋ ዞን ግምቢ ከተማ ተከብሯል።
በነገሌ ቦረና የሰንደቅ ዓላማ ቀን ሲያከብሩ የነበሩ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት "አባቶቻቸን የህይወት መስዋእትነት በመክፈል የሀገር ሉአላዊነት ያስከበሩት ለሰንደቅ ዓላማ ክብር ሲሉ ነው" ብለዋል፡፡
የከተማው ነዋሪ አቶ ባጫ ጂማ እንዳሉት ሰንደቅ ዓላማ ከሀገር ሉዓላዊነት መለያነቱ አልፎ የብሄር ብሄረሰቦች የእኩልነትና የአብሮነት ምልክት ጭምር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አባቶቻቸንን ለሰንደቅ ዓላማው ሲሉ በከፈሉት የአጥንት፣ የደምና የህይወት መስዋእትነት የተከበረች አገር በማቆየት ለትውልድ ማስረከባቸውንም አስታውሰዋል፡፡
"እኛም እንደ አባቶቻችን የአከባቢያችንና የአገራችንን ሰላም ነቅተን በመጠበቅና ሌት ተቀን በመስራት የለማች ሀገርና የተከበረ አገርና ሰንደቅ ዓላማ ለልጆቻችን እናስረክባለን" ብለዋል፡፡
በዓሉን ካከበሩት የከተማው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ማርያም አሬሮ በበኩላቸው ሰንደቅ ዓላማ የነጻነታችን፣ የኩራታችንና የአብሮነታችን ምልክት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የአብሮነትና የነጻነት ምልክታችን የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ አክብሮና አስከብሮ ለተተኪው ትውልድ በማስተላለፍ ረገድ የሴቶችም ድርሻ ጉልህ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የነገሌ ቦረና ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ዙቤዳ መሐመድ በበኩላቸው ለሰንደቅ ዓለማችን ክብር ስንል የሀገራችንና አከባቢያችንና ሰላም እንጠብቅ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።፡
በተመሳሳይ በአምቦ ከተማ በተከናወነው የሰንደቅ ዓላማ አከባበር ስነ-ስርዓት ለይ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ወርቅነህ ካባ ባደረጉት ንግግር "ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያ ህዝቦች የህብረ ብሄራዊ አንድነትና የሉዓላዊነት መገለጫ አርማ ነው" ብለዋል።
“ዜጎች ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት ለሰንደቅ ዓላማ በሚሰጡት ክብር ይገልጻሉ ያሉት ኮማንደሩ፤ ሰንደቅ ዓላማችን ኢትዮጵያውያን ለነፃነታቸው ሲሉ መስዋእትነት የከፈሉበት የሰላም ምልክት በመሆኑም መንከባከብና ማክበር ግድ ይላል ብለዋል፡፡
16ኛው የሰንደቅ አላማ ቀን በተመሳሳይ በነቀምቴ ከተማ አስተዳደርም ተከብሯል።
በስነ ስርዓቱም የነቀምቴ ከተማ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ፈዬራ ዱጋሳ "እኛ ኢትዮጵያውያን ድህነትንና ኋላቀርነትን በማስወገድ የህዝቦችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በልማት በማረጋገጥ ሰንደቅ ዓላማችንን ከፍ እናደርጋለን" ብለዋል።
በዚህ ዓመት የሚከናወኑ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑም "በሰንደቅ ዓላማችን ፊት ለፊት በመሆን ቃል እንገባለን" ሲሉም ተናግረዋል።
በምዕራብ ወለጋ ዞን ግምቢ ከተማ በተካሄደው የሰንደቅ ዓላማ ቀን አከባበር ላይም የዞኑ ዋና አስተዳደሪ አቶ ሰለሞን ታምሩ እንዳሉት በየዓመቱ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ስናከብር በሀገሪቱ ህዝቦች መስዋትነት የተገኘው አንድነታችንን አጠናክረን በማስቀጠል መሆን አለበት ብለዋል።
አክለውም ሰንደቅ ዓላማችን የሉዓላዊነታችን እና የህልውናችን ዋስትና በመሆኑም በዚሁ ልክ ተከብሮ ለትውልድ ሊሸጋገር ይገባል ብለዋል።
በክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች በተከበረው ሀገር አቀፉ የሰንደቅ ዓላማ ቀን የጸጥታ አካላት፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ተማሪዎች ተሳትፈዋል።