ቀጥታ፡

የሰንደቅ አላማ ቀንን ስናከብር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅምን በዘላቂነት የማስከበር መርህን ይበልጥ በማጠናከር ነው-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2016 (ኢዜአ)፡-የሰንደቅ አላማ  ቀንን  ስናከብር ኢትዮጵያ በምትወከልባቸው የዓለም ሀገራት ላይ  በዲፕሎማሲው መስክ  ብሄራዊ ጥቅሟን በዘላቂነት የማስከበር መርህን ይበልጥ በማጠናከር ነው ሲሉ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ገለጹ።

16ኛው የሰንደቅ አላማ ቀን ''የሰንደቅ አላማችን ከፍታ ለህብረ ብሄራዊ አንድነታችንና ሉአላዊነታችን ዋስትና ነው'' በሚል መሪ ሃሳብ በመላው ኢትዮጵያ እየተከበረ ይገኛል፡፡


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣አምባሳደሮችና የተቋሙ ሰራተኞችም በዓሉን በጋራ አክብረዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን በዚሁ ወቅት፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ በምትወከልባቸው የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ መድረኮች ሰንደቅ አላማዋ ከፍ ብሎ እንዲታይና እሴቶቿ እንዲተዋወቁ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም የሰንደቅ አላማ ቀን ሲከበር ስለሰንደቅ ዓላማ ምንነት ክብርና ትርጓሜ በተገቢው መንገድ ለመረዳት እንዲሁም ለሉዓላዊነት ለነጻነትና ክብር የተደረገውን እና እየተደረገ ያለውን ተጋድሎ እውቅና ለመስጠት ነው ብለዋል።

በመሆኑም ይህ ቀን ሲከበር ኢትዮጵያ በመወከል በዓለም ሀገራት ተሰማርተው ያሉ ዲፕሎማቶች ብሔራዊ ጥቅምን በዘላቂነት የማስከበር መርህ ይበልጥ ለማጠናከር የምንተጋበት ወሳኝ ወቅት ነው ብለዋል። 

''ቀደምት አባቶች በክብር ያሻገሯትን ሰንደቅ ዓላማ የጸናች ሉዓላዊት ሀገር ሆና እንድትቀጥል የሁሉም ዜጎች ሀላፊነት ነው'' ሲሉም አክለዋል።

የሰንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ የጥቅምት ወር በገባ የመጀመሪያ ሰኞ ይከበራል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም