ቀጥታ፡

ተተኪው ትውልድ ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ኩራትና ምልክት መሆኑን ተገንዝቦ ተገቢውን ክብር ሊሰጥ ይገባል - የአገር ሽማግሌዎች

አዳማ፤ ጥቅምት 05/2016  (ኢዜአ) ፦ተተኪው ትውልድ ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ኩራትና ምልክት መሆኑን ተገንዝቦ ተገቢውን ክብር ሊሰጥ እንደሚገባ የአዳማ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎችና የአስተዳደሩ አመራር አባላት ገለፁ ።

የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን  ''የሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ ለሕብረ - ብሔራዊ አንድነታችንና ሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው'' በሚል መሪ ሐሳብ  በአዳማ ከተማ ዛሬ ተክበሯል። 

የአዳማ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች ጉባኤ አባል የሆኑት አቶ ፋይሳ መገርሳ በዚሁ ጊዜ  "ሰንደቅ ዓላማችን ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ የምትወከልበት ምልክታችን ነው" ሲሉ ለኢዜአ ገልጸዋል።

አትሌቶቻችን በሩጫ ድል ሲያደርጉ ሰንደቅ ዓላማችንን ከፍ በማድረግ የኢትዮጵያ ኩራት መሆኑን የሚገልፁበት አርማችን ነው" ያሉት አቶ ፈይሳ፤ የአሁኑ ትውልድም የሀገርና የዜጎች ኩራትና ክብር መሆኑን ተገንዝቦ ተገቢውን ክብር መስጠት እንደሚገባው ተናግረዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ሃጂ ሁሴን ሃሞም "ሰንደቅ አላማ የሉዓላዊነታችን ምልክት ከመሆኑም ባለፈ በዓለም ላይ የምንታወቅበት አርማችን ነው" ብለዋል።

 ትውልዱ ሰንደቅ ዓላማችን  የነፃነትና ሉዓላዊነት ምልክት መሆኑን ተገንዝቦ ጠዋት ሲወጣና ማታ ሲወርድ ተገቢውን ክብር መስጠት አለበት ብለዋል።

"ሰንደቅ ዓላማችን የኢትዮጵያ ስም በዓለም አደባባይ የሚጠራበት፤ የማንነታችን አርማ በመሆኑ ተገቢውን ክብር ልንሰጠው ይገባል" ያሉት ደግሞ አቶ ግርማ ሰንበቶ ናቸው።

ሰንደቃችን "የነፃነታችን፣ የዕኩልነታችንና ህብረብሔራዊነታችን ማሳያ ነው" ያሉት አቶ ግርማ፤ በየቀኑ በተቋማት ሲሰቀልና ማታ ሲወርድ ማክበር አለብን ብለዋል።

በተለይም የአሁኑ ትውልድ ሰንደቅ ዓላማችን አባቶቻችን የተሰውለት የኢትዮጵያ ዓርማ መሆኑን በመገንዘብ ተገቢውን ክብር መስጠት አለብን ያሉት ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ሃደ ሲንቄ ዘውዴ ገመዳ ናቸው።

የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ሂንሴኔ ሙሐመድ በበኩላቸው የአሁኑ ትውልድ ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ክብርና ምልክት መሆኑን በአግባቡ እንዲረዳና ተገቢውን ክብር እንዲሰጠው ማስቻል አለብን ብለዋል።

"ሰንደቅ ዓላማችንን ማክበር  ሉዓላዊነታችንን ማክበር ነው" ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፤ የዘንድሮውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን ስናከብር ቀኑን ማሰብ ብቻ ሳይሆን ሀገሩንና ባንዲራውን የሚወድ ትውልድ ለመገንባት ቁርጠኛ መሆን አለብን ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም