ቀጥታ፡

የሰንደቅ ዓላማን  ክብር በመጠበቅ  ድህነትን ታሪክ ለማድረግ በጋራ ልንረባረብ  ይገባል-  የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር 

ጋምቤላ፤ ጥቅምት 5 / 2016(ኢዜአ)፦ የሰንደቅ ዓላምን ክብር በመጠበቅ ያለንን  ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ወደ ልማት ለውጠን  ድህነትን ታሪክ ለማድረግ በጋራ ልንረባረብ ይገባል  ሲሉ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር  አቶ  ቴንኩዌይ ጆክ አመለከቱ።

 "የሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንና ለሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው" በሚል መሪ ሀሳብ 16ኛ ው  ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በጋምቤላ ከተማ ተከብሯል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ በክብረ በዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር ፤ ኢትዮጵያ በጀግኖች አባቶች ተጋድሎ ሉዓላዊነቷ ተጠብቆና ዳር ድንበሯ ተከብሮ የቆየች የገናና ታሪክ ባለቤት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል። 

የማንነታችንና የህብረ ብሄራዊ አንድነታችን መገለጫ የሆነውን የሰንደቅ ዓላማን ክብር በመጠበቅ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ታሪክ ለማድረግ በጋራ ልንረባረብ  ይገባል ብለዋል።

በተለይ ወጣቱ ትውልድ ከአባቶቹ የተረከባትን ሀገሩንና የማንነቱ መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓለማውን በመጠበቅ ለአካባቢውና ለሀገሩ  የብልጽግና ጉዞ እውን መሆን ጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ሰንቅድ ዓላማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና  ህዝቦች የነፃነት፣ የአብሮነት፣ የአንድነትና የህብረ ብሄራዊ መገለጫ ዓርማ በመሆኑ ተገቢን ክብር በመስጠት ለቀጣዩ ትውልድ ልናስተላልፍ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

በዓሉ በየዓመቱ መከበሩ ህብረ- ብሔራዊ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን ለማጠናከር ካለው ፋይዳ በተጨማሪ ለወጣቱ ትውልድ የሰንደቅ ዓላማን ትርጉምና ክብር እንዲገነዘብ በማድረግ ረገድም ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

 

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አቶ ኮንግ ጋድቤል በሰጡት አስተያየት፤ ሰንደቅ ዓላማ የማንነት፣ የአንድነታችንና  የብሮነታችን መገለጫ ዓርማ መሆኑን ተናግረዋል።

ዕለቱን ሲያከብሩ በአብሮነት የሀገራዊ ስሜትን በሚያጠናከር መልኩ መሆኑን    ገልጸዋል።

ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ክብርና ማንነት መገለጫ  መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የበዓሉ ታዳሚ አቶ ጆን ኡጃንግ ናቸው።

በክብር በዓሉ ላይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ፣ የፌዴራልና የክልል የፖሊስ አባላት የሰልፍ ትርኢት አሳይተዋል።

የክልሉ አመራሮችና የበዓሉ ታዳሚዎች ለአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላምና ልማት ተግተው ለመሰራት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፤ የሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ-ሥርዓትም ተካሄዷል።

የሰንደቅ ዓላማ ቀን  የጥቅምት ወር በገባ የመጀመሪው ሰኞ በሀገር አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ እንደሚከበር በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 863/2006 አንቀጽ 2 ተደንግጎ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም