ቀጥታ፡

በሰንደቅ ዓላማችን ሥር ተሰባስበን የኢትዮጵያን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት እናፀናለን-የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 5/2016 (ኢዜአ)፦ በሰንደቅ ዓላማችን ሥር ተሰባስበን የኢትዮጵያን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት እናፀናለን ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ መላው ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለ16ኛ ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን አደረሳችሁ ብሏል፡፡

ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፦

በሰንደቅ ዓላማችን ሥር ተሰባስበን የኢትዮጵያን ሕብረብሔራዊ አንድነት እናፀናለን!

መላው ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለ16ኛ ብሔራዊ የሰንደቅዓላማ ቀን አደረሳችሁ!

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነታችን ምልክት፣ የነፃነታችን አርማና የክብራችን መገለጫ ነው፡፡ ሰነደቅ ዓላማችን ከትውልድ ትውልድ የተሸጋገረ፣ የጀግኖች አባቶቻችን የደማቸው ፍሳሽ፤ የአጥንታቸው ክሰካሽ እንዲሁም የመስዋዕትነት ውጤት የሆነ የድል ሰንደቅ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ፣ የሕዝቦቾን ነፃነትና ክብር ለማጽናት ጀግኖች ኢትዮጵያዊን ለሰንደቅዓማችን ፍቅርና ክብር በአንድነት መስዋትነት ከፍሏል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ በትውልድ ቅብብሎሽ ለሉዓላዊነታችን የተከፈለ መስዋዕትነት እና ሕብረብሔራዊ አንድነታችንን የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ የሀገራችን ሉዓላዊነት ምልክት የሆነው የሰንደቅዓላማችን ፀንቶ የቀጠለው ኢትዮጵያዊያን በአንደነት በከፈሉት መስዋእትነት ነው፡፡

ዛሬ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ 16ኛው የብሔራዊ ሰንደቃላማ ቀን “የሰንደቅዓላማችን ከፍታ ለሕብረብሔራዊ አንድነታችንና ሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው!” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል፡፡

የዘንድሮውን የሰንደቅዓላማ ቀን ስናከብር ሕብረብሔራዊ አንድነታችን ሉዓላዊነታችን እና የህልውናችን ዋስትና መኾናቸውን ታሳቢ ልናደርግ ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ሕብረብሔራዊ ሀገር ናት፡፡ እጅግ ብዙ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶች፣ መልከአምድርና የአየር ጠባዮች፣ ፍላጎቶች፣ አስተሳሰቦች፣ እምቅ ሀብቶች ያላት ብዝኃነት መገለጫዋ የኾነች ዕፁብ ድንቅ ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያችን ብዙ ኾና አንድ፤ አንድ ኾና ደግሞ ብዙ ነች፡፡

በዛሬው ዕለት የሰንደቅዓላማ ቀንን ስናከበር እነዚህን ኹለት የሀገራችንን ምሶሶ የኾኑ መገለጫዎች መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሕብረብሔራዊ አንድነታችን ሲጠናከር የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትም በፅኑ መሠረት ላይ ይቆማል፡፡ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓለማ ክብር ከፍ ይላል፡፡ የሰንደቅዓላማችን ከፍታ በዘላቂነት የሚቀጥለው ሕብረብሔራዊ አንድነታችንን ለማጠናከር በሚከናወነው ጠንካራ ሥራ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ከትላንት እስከ ዛሬ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ነፃነት በደማቸው ጠብቆ አቆይቷል፣ ሰንደቅዓላማችንን ከፍ አድርጓል፡፡

የዛሬ ትውልድ በአባቶቹ የህይወት መስዋእትነት ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ የቆየችውን ሀገር በላቡ ማፅናት ይጠበቅበታል፡፡ ዛሬ ላይ ሉዓላዊነታችን በዘላቂነት ሊረጋገጥ የሚችለው ሀገራችንን ከልመና ነፃ ስናወጣት ነው፡፡

ይህ የሚረጋገጠው ትውልዱ ያለበትን እዳ ተገንዝበው በተሰማራበት ዘርፍ ሁሉ በላቡ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ሲያረጋግጥ ነው፡፡

የሀገራችን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ሲኾን የማንነታችን መገለጫ፣ ሰንደቅዓላማችንም ልዕልናው ይጨምራል፡፡

መላው ኢትዮጵያዊያን ለሀገራችን ሰንደቅዓላማ ያለንን ክብርና ፍቅር ሕብረብሔራዊ አንድነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን ሊያስጠብቁ በሚችሉ ክንውኖች ላይ በመሳተፍ በተግባር ማሳየት ይገባናል፡፡

የሀገራቸውን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ መስዋዕትነት የሚከፍሉትን አካላት እንደ ወትሮው ኹሉ በማክበር ለሰንደቅዓላማችን ዘብ መቆማችንን በተጨባጭ ማስመስከር ይጠበቅብናል፡፡

ሕብረብሔራዊ አንድነታችንንና ሉዓላዊነታችንን አፅንተን የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ በከፍታ እናውለበልባለን!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም